በፓርላማው ተልእኮ ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ስራዎችን እናዘምናለን -አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

78

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)በፓርላማው ተልእኮ ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ስራዎችን እናዘምናለን ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ሁለተኛው አመታዊ የፓርላማ የምርምር ኮንፍረንስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዷል።

የምክር ቤቱን አሰራር በምርምር ላይ በማስደገፍ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር የሚቆጣጠራቸው ተቋማትም በዚሁ አግባብ ታግዘው እንዲሰሩ የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የጥናቱ የሰነዶች ትንተና ላይ ከሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ከፖለቲካ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ከዩንቨርሲቲ ምሁራን በተገኙ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የተከናወነ መሆኑ ተገልዕጿል።

በዚህም፣ ''ውጤታማ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የዳኝነት አካል ግንኙነት፣ለዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት፤''ፓርላሜንታዊ ቁጥጥር ተጠያቂነትና የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ተዋንያን፣ስልቶች ፈተናዎችና የወደፊት አቅጣጫ'' በሚሉና የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ፓርላማውን ጨምሮ የተቋማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ምርታማና ውጤታማ ስራ ለማምጣት ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም በፓርላማው ተልእኮ ዙሪያ የተሻለ ክንውን እንዲኖር ምርምር በማካሄድ ስራዎችን እናዘምናለን ብለዋል።አፈ ጉባኤው በተለይም ህግ አውጪው በስራው ሂደት እስካሁን የመጣበት መንገድና አሁን አገሪቷ በደረሰችበት ደረጃ የአሰራር ለውጦች የሚያስፈልጉት ስለመሆኑም አንስተዋል።

የአደረጃጀት፣አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው ጋር የአሰራር ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ማመላከት የሚገባ በመሆኑ የምርምር ውጤቱ ወደ ተግባር ተቀይሮ ለአገር እድገት በሚጠቅም መልኩ እንደሚሰራበትም ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤የአገረ መንግስት ግንባታው የተሳካ እንዲሆን በምርምር የተደገፉ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተሻሉ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣የዜጎች ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ የህዝቡ አኗኗር እንዲቀየር ተቋማት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ምክር ቤቱ በአሰራር፣በህግ አወጣጡና በአፈጻጸሙ እንዲጠናከር ምርምሩ የጎላ ትርጉም አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራውን በማገዝ አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የጥናቱ አቅራቢዎች፤ የምርምር ውጤት ለምክር ቤቱ ግብዓት ከመሆን ባለፈ ምክር ቤቱ የሚከታተላቸውን ተቋማት ጭምር የሚጠቅም እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም