በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገቡ

93

አሶሳ፤ ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2014 በጀት ዓመት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ኢንቨስትመንቱ  መነቃቃት እያሳየ ነው።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 375 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የሚያንቀሳቅሱት 375 ባለሀብቶች አብዛኞቹ በማዕድንና በግብርና ዘርፎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤  ከ54 ሺህ 800 በላይ ሄክታር መሬት መረከባቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ከ 44 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወገኖች  የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ባለሀብቶቹ በበጀት ዓመቱ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ 13 ቢሊዮን 176 ሚሊዮ 792 ሺህ ብር  ማስመዝገባቸውን አቶ አመንቴ አስታውቀዋል፡፡  

ሙስና፣አድሏዊነትና የተንዛዛ ቢሮክራሲ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ቢሮው በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 ሠላም ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አቶ አመንቴ፤ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም የሁሉም አካላት የጋራ ጥረትና መደጋገፍ እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ አብዱልማሙድ ኢብራሂም በክልሉ በተለይም በማዕድን ልማት የተገኙ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።

''የግብርናውን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ  ከመንግስት ጎን ቆመን ክፍቶችን በመሙላት የድርሻችንን መወጣት አለብን'' ብለዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ይዞ እየመጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አበባው ወንድማገኘው ናቸው።

በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አመልክተው፤ ከአዲስ አበባና ከአጎራባች ክልሎች ያለው የትራንስፖርት ግንኙነት ውስን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን እንዲችል  የክልሉ መንግስት የአካባቢውን ሠላም ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ለማድረግ በቁርጠኝት መስራት እንዳለበት ባለሀብቱ ገልጸዋል፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአባይ ወንዝን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችን፣ ሰፊ ለም መሬት፣ የወርቅ፣ እምነበረድ፣ ድንጋይ ከሰል፣ እጣንና የቆላ ቀርከሃ  ሀብቶች የሚገኙበት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም