ኢንተርፕራይዞች ያለባቸውን የመስሪያና መሸጫ ቦታ ችግር ለመፍታት ወጪ ቆጣቢ የመስሪያ ቦታ ግንባታ እየተካሄደ ነው

115

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያለባቸውን የመስሪያ ቦታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኢንዱስትሪ ፓርክ ደረጃ የሚሰራ ወጪ ቆጣቢ የመስሪያ ቦታ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ያዘጋጀውና ከ220 በላይ ኢንተርፕራይዞችን ያሳተፈ አገር አቀፍ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የተመረጡ ኢንተርፕራይዞችም ምርቶቻቸውን በተለያዩ አማራጮች ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እያስተዋወቁ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በመስሪያና መሸጫ ቦታ እጥረት እየተቸገሩ ነው።

በመሆኑም ችግሩን በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመፍታት በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የክላስተር ማዕከላት ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በጊዜያዊነት ከክላስተር ማዕከላት ግንባታ በተጨማሪ ወደስራ ያልገቡ ማዕከላትን መሰረተ ልማት በማሟላት ወደስራ እንዲገቡ ከማድረግ ባሻገር ከደረጃ በታች የሆኑ ማዕከላትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን በማንሳት።

የኢንተርፕራይዞች ቁጥርና የማምረት አቅም እድገትን ተከትሎ  የቦታ ፍላጎታቸው ስለሚያድግ በክልሎች የተለያዩ ወጪ ቆጣቢ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው ቦታ እንዲያገኙ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በሶማሌ ክልል ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ለዚህም በወረዳ ከተማ 50 ሄክታር፣ በመካከለኛ ከተሞች 100 ሄክታርና በትላልቅ ከተሞች ደግሞ 250 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን በማንሳት።   

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ለኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ ለማቅረብ ከሊዝ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በዓለም ባንክ ድጋፍ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚሰራጭ 11 ቢሊዮን ብር መመደቡንም በመጠቆም።

ኢንተርፕራይዞች በስፋት ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በማንሳት ዛሬ የተጀመረው ኤግዚቢሽንና ባዛርም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

በዚህም የተመረጡ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በተለያዩ አማራጮች ለዓም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎቻቸው የሚያስተዋውቁበት መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ይህም ምርቶቻቸውን ዩቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ የዲጂታል መንገዶች ለተጠቃሚዎች እንዲያስተዋውቁ ያግዛል ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሁሉም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ እንዲሆኑና የራሳቸውን  ሚና እንዲጫወቱ የዲጂታል ገበያ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርቶቻቸውን በመድረኩ እያስተዋወቁ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው መድረኩ በዓለም አቀፍ ገበያ ምርቶቻቸውን ተደራሽ ለማድረግና የገበያ እድላቸውን ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዞች እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩንም እንዲሁ።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከሰኔ 16 ቀን 2014 ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም