ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር መገናኛ ብዙሃን አዎንታዊ ሚና ሊወጡ ይገባል

93

አዳማ ሰኔ 17/2014ኢዜአ)… የህዝቦች እኩልነት ተከብሮ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ሚና በተገቢው መወጣት አለባቸው ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገነዘበ።

ምክር ቤቱ  በህብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታና ሐሰተኛ መረጃን በመታገል ረገድ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለሙያዎች ጋር  ዛሬ በአዳማ መክሯል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ኦሞድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች "የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን በመዋጋት የህዝቦች እኩልነትና አንድነት የተረጋገጠባት ሀገር መገንባት ይገባል"።

በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲጠናከርና እንዲዳብር መገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አወንታዊ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ምክትል አፈጉባኤዋ አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች የሀገራችን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታን በአግባቡ በመረዳት የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው "ለእውነትና ለበጎ ከቆመ ሀገርን ከአፍራሽ እንቅስቃሴ የመታደግ አቅሙ ከፍተኛ ነው" ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ ለሐሰተኛና እኩይ ተግባር ተገዥና ታዛዥ ከሆኑ ግን ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዚህም ተቋማቱና ባለሙያዎቹ ከሚለያዩን ጥቃቅን እሳቤዎች ወጥተው አንድ በሚያደርጉንና ሀገሪቷን ወደፊት ማራመድ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማተኮር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በተለይም ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግር ፈብራኪዎችና አሰራጮችን ተከታትለው ሊያጋልጡ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የመድረኩ ዓላማም የሚዲያ ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎች ከምክር ቤቱ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተግባቦት መፍጠር ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በምክር ቤቱ የህግ ባለሙያ አቶ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው ምክር ቤቱ በህዝቦች መካከል በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲጠናከር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የመገናኛ ብዙሃንና የዘርፉ ባለሙያዎች ዜጎች ህገ መንግስቱንና ፌዴራላዊ ስርዓቱን በትክክል ተገንዝበው በሀገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ከማስቻል አንፃር ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የተረጋጋችና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ሀገር እውን ለማድረግ ሁሉም በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ለአንድ ቀን በተሰናዳው በዚህ ውይይት የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች፣ አመራርና ባለሙያዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም