በዞኑ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ለበልግና መኸር እርሻ እየዋለ ነው

223

መቱ ሰኔ 17/2014 (ኢዜአ)... ምርትና ምርታማነት እንዳይቀንስና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያን እጥረት ለማካካስ በተሰራው ስራ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽሕፈት ቤቱ የሰብል ልማትና ዕፅዋት ጥበቃ ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ተፈሪ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት እንደ ሀገር ካጋጠመው የማዳበሪያ እጥረትና እንዲሁም የአፈር ለምነትና እርጥበት ለማቆየት ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።

አርሶ አደሩ በግብርና ልማት ባለሙያዎች ታግዞ በሰራው ስራም በዞኑ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ለበልግና ለመኸር አዝመራው እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢሉባቦር ዞን በዚህ ዓመት በበልግና መኸር እርሻ ከ135 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከአጠቃላይ መሬቱም እስካሁን 132 ሺህ 834 ሄክታሩ ታርሶ መዘጋጀቱንና  ከዚህም 80 በመቶው በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በበልግና መኸር ከሚዘሩ ሰብሎችም 35 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም ታርሶ የተዘራ መሆኑን አቶ ተፈሪ አክለው ገልፀዋል።

ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል በምግብ እህል ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዞኑ አርሶ አደሮች ናቸው።

በማዳበሪያ እጥረት ምርቱ እንዳይቀንስባቸውና የአካባቢውን እርጥበትና ልምላሜ ይዞ እንዲቆይላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያን በባለሙያ ታግዘው ሲያዘጋጁ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

በዞኑ የአሌ ወረዳ የሰጊ ባቂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለማ ባልቻ እንደገለፁት ከዚህ በፊት በማሳቸው ላይ ዘመናዊ ማዳበሪያን በመጠቀም ያርሱ እንደነበርና በዚህ ዓመት ግን እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ ትኩረታቸውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት አዙረዋል።

ለወደፊትም በተፈጥሮ ማዳበሪያው ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን ጉዳት በተፈጥሮ ማዳበሪያው ለማካካስ እንደሚሰሩ ነው አቶ ለማ የገለፁት።

በዚሁ በአሌ ወረዳ የሰጊ ባቂ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይርጋለም ጫሊ በበኩላቸው የማዳበሪያ ዋጋ ከነበረው በብዙ እጥፍ በመጨመሩ ፊታቸውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዞሩ እያስገደዳቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ጌታቸው አብዲሳ በዘንድሮው መኸር የሚያስፈልጋቸውን የመሬት ማዳበሪያ ለወረዳው ከተሰጠው ኮታ አንፃር ማግኘት እንደማይችሉ በባለሙያዎች ስለተነገራቸው በማሳቸው ላይ 70 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በ2014/2015 እየለማ ካለው የበልግና የመኸር እርሻ በአጠቃላይ እንደ ዞኑ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም