የመሬት ካሣ ትመና ሠራተኞች ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተያዙ

137

እንጅባራ ፤ ሰኔ 17/2014 (ኢዜአ) በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የአዲስ ቅዳም ከተማ አስተዳደር ሁለት የመሬት ካሣ ትመና ሠራተኞች "የመሬት ካሳ እንሰራላችኋለን" በሚል 97 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

ሠራተኞቹ  እጅ ከፈንጅ የተያዙት ትናንት ቀን አምስት ሠዓት አካባቢ  በከተማው በተለምዶ ኳስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ድርጊቱን ሲፈፅሙ መሆኑን የከተማዋ አሰተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ግርማ አለማየሁ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም የመሬት ካሣ ትመና ቡድን መሪና ባለሙያ የሆኑት ሠራተኞቹ ጉቦውን ሲቀበሉ የተደረሰባቸው ከመሬት ካሣ አገልግሎት ፈላጊ ግለሰቦች መሆኑን አስረድተዋል።

ሊያዙ የቻሉትም ፖሊስ ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ  ባደረገው  ክትትልና ቅንጅታዊ ስራ  መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም  የመሬት ካሣ ፈላጊ ሁለት የአንድ ቤተሰብ አባላት 97 ሺህ ብሩን ሰጥተው "የተሻሻለ የካሣ ግመታ" የሚል ባለሶስት ገጽ ደብዳቤ ከሠራተኞቹ ጋር ሲቀባበሉ ሊያዙ እንደቻሉ አመላክተዋል።

እንደ ምክትል ኮማንደሩ ገለፃ ፤ግለሰቦቹ ባለ 200 ብር ኖት 81 ሺህ 400 ብር፣ ባለ100 ኖት 10 ሺህ 600 ብር እና 5 ሺህ ባለ 50 ብር ኖት ከካሣ ክፍያ መፈጸሚያ መረጃ ጋር እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ግለሰቦቹ ጉዳያቸው ዛሬ ለህግ ቀርቦ ምርመራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በገንዘብ ከመግዛት ይልቅ እየሠጠ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ ህጋዊ ሆኖ ማግኘት የሚችለውን  አገልግሎት በገንዘብ ለማግኘት ከመሞከር በመቆጠብ  የስነምግባር ጉድለት ባለባቸው እንዳይታለል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም