የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያገዘ ነው

164

ጂንካ ፤ሰኔ 17/2014(ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያገዙ መሆናቸውን የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ አስታወቁ።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በፋውንዴሽኑ የሚተገበሩ የልማት ስራዎችን በስፍራው ተገኝተው በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤  ፋውንዴሽኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየሰራ ነው።

የብዘሀ-ህይወት ጥበቃና ኢኮ-ቱሪዝም፣ሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራትና በስርዓተ-ምግብ ዙሪያ  የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርፀው እየሰሯቸው ካሉት ተግባራት ይገኙበታል፡፡

ፋውንዴሽኑ በደቡብ ኦሞ ዞን  ሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎችም በዳሰሳ ጥናት በተለዩና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጠቅሙ እገዛዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም የተማሪዎች ምገባ፣የእናቶች፣የህፃናትና የጨቅላ ህፃናት ጤና እንክብካቤና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የማጎልበት ስራዎች  ዋነኞቹ ናቸው።

በወረዳዎች በሚገኙ አምስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ሴት ተማሪዎችን በትምህርታቸው ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችል የሴቶች የትምህርት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደጊያ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ስራዎቹ ለሁለት ዓመታት እንደሚቀጥሉ የገለጹት ወይዘሮ  ሮማን፤ የሴት ተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት፣ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን መከላከልና የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ያለባቸውን ሴቶች የሚደግፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወሊ ኃይሌ ፤ ፋውንዴሽኑ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን በመሆን እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

ፋውንዴሽኑ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።

በሐመር ወረዳ ከፋውንዴሽኑ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑ የዲመካ አንደኛ ደረጃ  ትምህርት ተማሪዎች መካከል ሰሊማ የሱፍ በሰጠችው አስተያየትት፤ በትምህርት ቤቱ ምገባ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቁርሳቸውን ሳይበሉ የሚመጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ይቸገሩ እንደነበር አስታውሳለች።

ምገባ ከተጀመረበት ወዲህ ግን ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ማድረጋቸውን ገልጻለች፡፡

ፋውንዴሽኑ የአጋዥ መፃሕፍትና የንፅህና መጠበቂያዎችን ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የዲመካ ሚሊኒየም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ጋይቶ ሲልቦ ናት።

ድጋፉ ሴት ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡና በተለያየ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ፋውንዴሽኑ ለሴት ተማሪዎች ካደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በትምህርት ቤቶቹ ያለውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የሚያግዙ በቴክኖሎጂ እገዛ በአየር ውስጥ ካለው እርጥበት ውሃን በመሰብሰብ በቀን 100 ሊትር ውሃ የሚያመነጩ  አምስት ማሽኖችን ማበርከቱም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም