በኮርፖሬሽኑ ለመኸር እርሻ ከ155 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሆኗል

86

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመኸር እርሻ 155 ሺህ 348 ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን አስታወቀ።

በአገሪቷ የምርጥ ዘር ግብዓት እጥረት ችግርን ለማቃለል ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ መሆኑንም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገር ደረጃ ካሉት 25 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መካከል የአዳማ እና አሰላ ቅርንጫፎች ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ ጉዳዮች አገልግሎት ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም፤ ኮርፖሬሽኑ በ22 የሰብል ዓይነቶች 69 የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

 

በኮርፖሬሽኑ መሬት፣ በኮንትራት ሰፋፊ እርሻ እና በአርሶ አደር መሬት በድምሩ 14 ሺህ 608 ሄክታር መሬት ላይ ዘር ማባዛቱን ተናግረዋል።

ለዘንድሮው የመኸር እርሻም አባዝቶ ካዘጋጀው 280 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እስካሁን 155 ሺህ 348 ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉ ተገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ በአገር ደረጃ በየዓመቱ ከሚያስፈልጉ የምርጥ ዘር ፍላጎት እስከ 30 በመቶውን እያቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለ2014 የመኸር እርሻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒት እና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ለተጠቃሚዎች ማቅረቡንም ገልጸዋል።   

በተጨማሪም የእርሻ መሣሪያዎችን ከውጭ በማስመጣት የሽያጭ እና የኪራይ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለመጪው የምርት ዘመን 365 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማባዛት ማቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአዳማና አሰላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች፤ ምርጥ ዘር እና የተለያዩ ኬሚካሎች ለአርሶ አደሮች እየደረሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የአሰላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እስካሁን 30 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ማሰራጨቱን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም 50 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን 15 ሺህ ኩንታል የጤፍ ዘር ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሮች ሊከፋፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም እስካሁን ከ100 ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካል ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን አስታውቋል።

አሁን ላይ 20 ሺህ ሊትር ኬሚካል የመድኃኒት ክምችት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮችም የተሻሻለ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ምርታማ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ምርጥ ዘር ከመጠቀማቸው በፊት ከ1 ሄክታር መሬት 18 ኩንታል የስንዴ ምርት ሲያገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ ምርጥ ዘር ከተጠቀሙ በኋላ ግን ምርቱ በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ማዳበሪያ ብቸኛ አስመጪ ሲሆን ግዢ ከተፈፀመው ውስጥ እስካሁን 92 በመቶ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እና ጂቡቲ ወደብ መድረሱን አስታውቋል፡፡

ለምርት ዘመኑ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለአርሶ አደሮች ከተሰራጩ አግሮ ኬሚካሎች በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ 300 ሺህ አግሮ ኬሚካሎች በኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም