ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከ5 ሺህ 800 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አስረከቡ

139

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 5 ሺህ 865 መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዛሬ አስረክበዋል፡፡

'ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ' በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በሚከናወነው የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማትና ዜጎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያሰባሰቧቸውን መጻሕፍት ዛሬ አስረክበዋል፡፡

መጻሕፍቱን የዩኒቨርሲቲውና የኮሌጁ አመራሮች ለአዲስ አበባ የባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ ፈይሳ ፈለቀ ነው ያስረከቡት፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 4 ሺህ 334 መጻሕፍትን ለአብርሆት አበርክቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ጀማል የሱፍ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸው መጻሕፍት የተለያዩ የምርምር፣ የፍልስፍና እንዲሁም የታሪክ ይዘት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 1 ሺህ 531 መጻሕፍትን አስረክቧል፡፡

የኮሌጁ ዲን ግሩም ግርማ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፤ መጻሕፍቱ ከተማሪዎች፣ ከሰራተኞች እና ከተቋሙ ወዳጆች የተሰበሰቡ ናቸው፡፡

የመጻሕፍቱ ይዘትም በአውቶሞቲቭ፣ በማፋክቸሪንግ፣ ከኤሌትሪካል ምህንድስና እንዲሁም በርካታ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የሚያሰለጥኗቸው የሙያ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የባህል ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት ላደረጉት አበርክቶ አመስግነው በቀጣይም በሚደረገው የትውልድ በእውቀት የማነፅ ሂደት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ መረጃ በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ ስለሺ ሻምበል የተባሉ ግለሰብ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ(አባነፍሶ) በኢትዮጵያ የሰሯቸው የጀብዱ ታሪኮች ላይ ያዘጋጁትን መፅሐፍ በተወካያቸው አማካኝነት አስረክበዋል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተ-መጻሕፍት ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍትን መያዝ የሚችል ሲሆን 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የመጻሕፍት መደርደሪያም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም