አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገብ የቻለ አኮኖሚ መገንባት አስችሏል

171

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎቸን ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገብ የቻለ አኮኖሚ መገንባት ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አህመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተገኙ ለውጦችን በማጠናከር ችግሮችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መስቀመጡንም ነው የተናገሩት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰሞኑን በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና የሰላም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ አቅጣጫ መስቀመጡ ይታወሳል፡፡

በዚህም በተለይ በኢኮኖሚው መስክ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በአጭር ጊዜ ለውጥ ማስመዝገብ አስችሏል።

በዚህም የኢትዮጵያን የእዳ ጫና መቀነስ፣ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የአገር ውስጥ ገቢንና የወጪ ንግድን መጨመር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በአንጻሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች መከሰታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ ችግሮቹን ተቋቁሞ ተከታታይ እድገት ያስመዘገበ ኢኮኖሚ መገንባት አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ንረት ኢትዮጵያንም እየፈተናት መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ምርታማነትን በመጨመር፣ የውጪ ንግድን ይበልጥ በማሻሻልና የአገር ውስጥ ገቢን ከፍ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰቱ ፈተናዎችን ለመቋቋም መስራት እንደሚገባ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ላይ ከቡና በተጨማሪ እንደ አቮካዶ ያሉ የግብርና ምርቶች በወጪ ንግዱ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል።

በአጠቃላይ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ከወዲሁ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች አገር አቀፍ መልክ እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅጣጫ ማስቀመጡን አንስተዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሁሉም ክልሎች ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም በተለይ የፋይናንስ ዘርፍን ተወዳዳሪና ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርግ የሪፎርም ስራ በማከናወን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ይሰራል ብለዋል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያን የብድር ጫና የሚቀንሱና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚጨምሩ የለውጥ ሰራዎች እንደሚደረጉም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም