ግሎባል አሊያንስ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚያካሂደው የሎግያ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

73

ሰመራ፣ ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ግሎባል አሊያንስ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በአፋር ክልል ውስጥ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚያካሂደው የሎግያ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተገለጸ።

የግንባታ ሂደቱን የግሎባል አሊያንስና የአፋር ልማት ማህበር የስራ ሃላፊዎች ትናንት ጎብኝተዋል።

በአፋር ልማት ማህበር የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ወንደሰን አለምነዉ እንደገለጹት፤ የማስፋፊያ ግንባታው 65 በመቶ ደርሷል።

የግንባታ ዕቃዎችና ተያያዥ ነገሮች ላይ የዋጋ ጭማሪ ቢያጋጥምም ማስፋፊያውን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በታቀደው መሰረት ስራው በመጪዉ ነሐሴ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የአፋር ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን ሰዲቅ በበኩላቸዉ የትምህርት ቤቱ ማስፊፊያ አሸባሪው ህወሃት ከፍቶት የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ተማሪዎች የተፈጠረዉን መጨናነቅ ለማቃለል ያለመ እንደሆነ አንስተዋል።

May be an image of outdoors

ማስፋፊያው ለመጪው አመት የትምህርት ዘመን ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዋጋ መጨመር የፈጠረውን ተጽዕኖ በመቋቋም ማስፋፊያውን ለማጠናቀቅ ከግሎባል አሊያንስ አመራሮች ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያ ተጠሪ አስቲስት ደሳለኝ ሃይሉ በቀጣይ ለትምህርት ቤቱ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የተጀመረው የማስፋፊያ ግንባታ ለአገልግሎት እንዲበቃ ግሎባል አሊያንስ ዳያስፖራውን በማስተባበር እንደሚሰራ ገልጿል።

በግሎባል አሊያንስ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የትምህርት ቤት የማስፋፊያ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለሁለት ብሎክና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያካትተ ሲሆን ግንባታው የካቲት 04 ቀን 2014 ዓ.ም የተጀመረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም