የተቋማቱ ጥናትና ምርምሮች አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማበልፀግና የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንዳለባቸው ተጠቆመ

117

ደብረብርሃን፣ ሰኔ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማበልፀግና የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት እንደሚጠቅባቸው ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ 'ተግባር ተኮር ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥ!' በሚል ሃሳብ 12ኛው የምርምር ሲምፖዚየምና ሦስተኛው የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት አገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በመድረኩ እንዳስገነዘቡት፤ በተቋማቱ በምሁራን የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ የህዝቡን ችግሮች ሊፈቱ ይገባል።  

ምርምሮች የአካባቢውን ህዝብ በማሳተፍ መካሄድ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ "ለዚህም አገር በቀል እውቀቶችን መጠቀም ይገባል" ብለዋል።

የምርምር ስራዎች ፈጥነው የሚተገበሩና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃና በቴክኖሎጂ ሽግግር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መምህራንና ተማሪዎች  ዕውቀታቸውን በተግባር በመቀየር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ  መልካም መደላድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

ምርምሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ አዲስ የምርምር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራዎች በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር እንዲደገፉና እውቀት ተኮር የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አዝመራ አየሁ፤ ባለፉት ዓመታት 580 የሚደርሱ የምርምር ስራዎች ቢካሄዱም አብዛኛዎቹ የማህበረሰቡን ችግሮች የመፍታት ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት ግን የማህበረሰቡን ችግር የሚያቃልሉ እንዲሆኑ በመደረግ ላይ ነው" ያሉት ዶክተር አዝመራ፤ ዘንድሮ 77 የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በኢንቨትስትመንት አዋጭነት፣ በምግብ ዋስትና በጤና ላይ እንዳተኮሩና 14 ቱ ተጠናቀው ወደ ትግበራ መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም