የህወሃት ሽብር ቡድን የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ ከልክሏል

93

በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ መንግስት ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል። ከተለያዩ አለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም አስፈላጊ መሰረታዊ ድጋፎች በየብስም በአየርም ሲያጓጉዝ ቆይቷል።

አሸባሪው ቡድን ይህንን የመንግስትን ጥረት ጥላሸት ለመቀባትና የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመንዛት ሲል ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብአዊ ድጋፎች የሚገቡበትን ሂደት ለማስተጓጎል በተደጋጋሚ ሞክሯል።

በየብስ የሚገቡትን ሰብአዊ ድጋፎች ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርሱ መንገድ በመዝጋትና የእርዳታ ማስተላለፊያ ኮሪደሮች አካባቢ ትንኮሳ በመፈጸም ከራሱ የፕሮፖጋንዳ ስሌት ባሻገር ለትግራይ ህዝብ ግድ እንደሌለው በተግባር እያሳየ መጥቷል።

በሽብር ቡድኑ በኩል የሚመጡ እንቅፋቶችን በመቋቋም መንግስት አስፈላጊውን ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል።

ሆኖም አሁን መንግስት ያመቻቸውና በየቀኑ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች የሚላክበትን የአየር በረራ የሽብር ቡድኑ መከልከሉና ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ ማድረጉ ታውቋል።

ይህ የህወሃት የሽብር ቡድን እርምጃ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ የሃሰት ፕሮፖጋንዳው መሳሪያ ከማድረግ ውጪ ሌላ አላማ እንደሌለው ዳግም በተግባር የሚያረጋግጥ ነው።

ይህንን የሽብር ቡድኑን ውሳኔ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የክልከላውንም ምክንያት እንዲያጣራ መንግስት መልእክቱን ያስተላልፋል።

በተጨማሪም መንግስት እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም