ከ2010 አስከ 2013 በጀት ዓመት ኦዲት ግኝትን ለማስተካከል ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ጥረት አበረታች ነው

99

ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ከ2010 አስከ 2013 በጀት ዓመት ኦዲት ግኝትን ለማስተካከል ያደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ገለጸ።

ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን የግዥ አፈጻጸም ስርዓት ከ2010 እስከ 2013 በጀት ዓመት ያለውን ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ተመልክቷል።

በመሆኑም የኦዲት ግኝትን ለማስተካከል ያደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል።

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ፤ ኮርፖሬሽኑ የኦዲት ግኝት ለማስተካከል ያከናወናቸው ስራዎች አበራታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኦዲት ለመደረግና ለማስተካከል ያደረገውንም አድንቀው ለሌሎች የልማት ድርጅቶች እንደ ሞዴል ሊወሰድ የሚችል ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ እያደረገ ያለው ተግባርም በጥሩ መልኩ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ከወቅቱ ጋር የሚሄድ የግዥ መመሪያና ደምብ በማውጣት የሚሰሩትን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለመከውን በሚያግዝ መልኩ የማሻሻሉ ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፌዴራል ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ ተቋሙ የግዥ መመሪያውን ዘመናዊ በማድረግ በኩል መስራት እንዳለበት ጠቅሰው የራሱን ውስጥ ቁጥጥርም ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

በኦዲት የተገኙ ክፍተቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችን ለይቶ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ከምክር ቤቱ የተሰጠውን ግብረ መልስ ተቀብለው በቀጣይ ያሉትን ውስን ክፍተቶች ለማስተካከል ይሰራል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በ2012 በጀት ዓመት የተገኙትን የኦዲት ግኝቶች መሰረት በማድረግ ሪፎርም በተቋሙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሲስተም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተሰሩ ይገኛል እስከ አሁንም ጥሩ ስራ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ግዥ የሚፈጽመው በቦርድ ሲወሰን መሆኑን ጠቁመው የተወሰኑ ግዥዎች በፕሮፎርማ አማካይነት እንደሚፈጸሙ ጠቅሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶችን በጊዜ የመጨረስና በአገር ደረጃ በትላልቅ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል ይህን የሚመጥን ሪፎርም እየሰራን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም