በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መስራት ይገባል- የአውሮፓ ህብረት

84

ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መስራት እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ ገለጹ።

ኮሚሽነሩ በሱማሌና ትግራይ ክልሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በስፍራው በመገኘት ጎብኝተዋል።

የጉብኝታቸውን ማጠናቀቅ አስመልቶም ለሀገር ውስጥና ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንንና ከክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው በተለይም የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻሉን ጠቅሰው በቀጣይም እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

በሱማሌ ክልል በነበራቸው ጉብኝትም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን አስታውሰው ድርቁ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን ገልጸዋል።

በድርቁ ሳቢያ በተለይም ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን እንደተመለከቱ ጠቅሰው ከሚቀርበው የእለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በመቐሌ ከተማ ተገኝተውም ባካሄዱት የሁለተኛ ቀን ጉብኝትም በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ምልከታ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ቆይታቸው የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እየገቡ ሲገቡ መመልከታቸውን አስታውሰው የመንግስትን ጥረት በማድነቅ ሰብአዊ አቅርቦቱ መሻሻል እያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም