የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳ ውጤት እየተመዘገበበት ነው

215

ጂንካ ሰኔ 15/2014(ኢዜአ)የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የአጋር ድርጅቶች ቅንጅት ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች በሃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን እየተከናወኑ ያሉ የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት የጤና ልማት ሥራዎችን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ያለመ የንቅናቄ ኮንፍረንስ በመካሄድ ላይ ነው።

በኮንፍራንሱ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ስለሺ ጋሩማ እንዳሉት በጤናው ዘርፍ ለማሳካት ከታለሙ ዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት መቀነስ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረትም አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት የነበረውን የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት ከ50 እስከ 70 በመቶ በመቀነስ የአጋር አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ወይዘሮ ዘቢዳር ቦጋለ በበኩላቸው የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥም ሴቶችን ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ማህበራዊና ልማዳዊ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ለማስቀረት ልዩ ትኩረት መስጠት ያሻል ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ የሴቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከመንግሥት ጎን በመሆን እያደረገ ላለው ተምሳሌታዊ አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

ፋውንዴሽኑ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

የሃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ፋውንዴሽኑ በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ስርዓተ ምግብና የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ላይ ይሰራል።

የአከባቢ ጥበቃና ኢኮ-ቱሪዝምም የፋውንዴሽኑ የትኩረት መስክ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በሀገሪቱ  በተለያዩ አካባቢዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት በስፋት በሚታይባቸው እንደ ሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች ባሉ አከባቢዎች ከጤና ተቋማትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ለዚህም ፋውንዴሽኑ በተለይም የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ማስፋፋት ትኩረት መስጠቱንና ሥራውን ስኬታማ ለማድረግም ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ በተመረጡ ጤና ጣቢያዎች የህክምና ቁሳቁስ በማሟላትም እገዛ እያደረገ መሆኑን ወይዘሮ ሮማን ተናግረዋል።

ለነፍሰ-ጡር እናቶች የቅድመ ወሊድና የድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ፣ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ ላይ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የማህፀን በር ካንሰር፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የአባላዘርና ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንዲሁም የህፃናት መቀንጨርን ለመከላከልም ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አታ መምሪያው ከፋውንዴሽኑና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት በሚያከናውናቸው የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ ተግባራት አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ የቅድመ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎት እንዲሁም በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎትና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከ80 በመቶ በላይ ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል።

የሃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን በጤና ዘርፍ ተጠቃሚ ካደረጋቸው ሴቶች መካከል የሐመር ወረዳ የኤሪያ- ቃይሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጎይቲ ፋኮ አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ጎይቲ እንደሚናገሩት ቀደም ሲል አከባቢያቸው ራቅ ያለ በመሆኑ እናቶች ወደ ጤና ጣቢያ በመምጣት ከመውለድ ይልቅ ቤት ውስጥ በመውለድ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ ነበሩ።

በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን እስከማጣት የሚደርሱ እንደነበሩም በማስታወስ።

አሁን ላይ ድርጅቱ ራቅ ባሉ ቀበሌዎች የሚገኙ ነፍሰ-ጡር እናቶች በጤና ጣቢያዎች በሚገኙ የእናቶች ማቆያ ውስጥ በመሆን ክትትል እየተደረገላቸው እንዲወልዱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በጤና ጣቢያው ልጃቸውን ለመውለድ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ኮንፍረንሱ እየተካሄደ ያለው "የተቀናጀ የጋራ ጥረት ለፈጣንና ተመጣጣኝ የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት ጤና ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በኮንፍረንሱ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም