በሐረማያ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

115

ሐረር ፤ ሰኔ 15 /2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያ ከተማ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ዋለ።

መነሻውን ድሬዳዋ ያደረገ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 07711 ኦሮ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ   የኮንትሮባንድ ዕቃውን ጭኖ ሐረር ለማስገባት እያጓጓዘ በሐረማያ በተለምዶ ገንደ ቆሬ በሚባለው አካባቢ እንደደረሰ ትናንት ሌሊት መቆጣጠር መቻሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ገልጸዋል።  

የሐረማያ ከተማ የጸጥታ ሃይል ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ባደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ተሽከርካሪው ላይ ተጭነው የነበሩ የመኪና ጎማ፣ጨርቃ ጨርቅ ፣የሞባይል ቻርጀርና ሌሎችም ቁሶች ማግኘት እንደተቻለ አስረድተዋል።

በቁጥጥር ስር የዋለው የኮንትሮባንድ ዕቃው ለሐረር ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ገቢ መደረጉንም  ተናግረዋል።

ኮንትሮባንዱን የጫነው ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ፤አሽከርካሪው ለጊዜው ሸሽቶ ቢያመልጥም ለመያዝ ፖሊስ በክትትል ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንና ሆኖም  በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት የሚሳተፉትን  አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

ኮንትሮባንድና ህገ ውጥ ንግድ  የሀገር ኢኮኖሚ የሚጎዳ በመሆኑ በመከላከሉ ረገድ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኢንስፔክተሩ  አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም