ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የፀጥታ አካላት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተጠየቀ

147

ጅግጅጋ፣ ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ተናገሩ። 

ህገ-ወጥ የንግድና ኮንትሮባንድ ለመከላከል  በጅግጅጋ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው  የንቅናቄ መድረክ ሲጠናቀቅ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ እንዳሉት፤  በድሬዳዋ፣ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ቢኬና ሞያሌ አካባቢዎች ኮንትሮባንዲስቶች ህገ ወጥ ስራ የሚሰሩባቸው ቦታዎች አሉ።

የጸጥታ ሃይሉ በሚፈለገው ልክ ተቀናጅቶ መስራት ባለመቻሉ ህገወጥ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች መቆጣጠር አለመቻሉን ገልጸው፤ ኮንትሮባንድን ለመከላከል ፀጥታ አካላት የሚታይባቸው የቅንጅታዊ አሰራር ችግር በመፍታት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የፀጥታ አካላት የማይደርሱበት የኮትሮባንድ ማከማቻና ህገ ወጥ ስራ የሚሰራበት ቦታ ከዚህ በኋላ አይኖርም" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፀጥታ አካላት ኮንትሮባንዲስቶችን የመየለትና እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ህግን በተከተለ አግባብ ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የተቋቋመው የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ሀይል አካላትን ያካተተ እቅድ አዘጋጅቶ ለመተግበር በጋራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሱማሌ ክልል  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው፤ ኮንትሮባንድን እና ህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተዋንያን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በአግባቡ በማጥናት እና በመለየት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ኮንትሮባንድ የትውልድ ፀር መሆኑን በጋራ ለመከላከል የኃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ አመራሮችና የፀጥታ አካላት መግባባት የደረሱበት ነው ያሉት ደግሞ የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን የህግ ህግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ  ናቸው።

በህገ ወጥ ድርጊት ተባባሪዎች ላይ  የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የመለየት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤  ኮሚሽኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ተገቢውን ስራ እንዲያከናወን የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።

"ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት" በሚል በተዘጋጀው  የንቅናቄው መድረክ  የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን ሀገራዊ ራዕይ  እውን እንዲሆን የድርሻውን  ለመወጣት ባለፉት ዓመታት  ያስመዘገባቸው ለውጦች የተመለከቱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በንቅናቄው  መድረክ ከፌዴራልና  ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም