ባለፉት 11 ወራት ከወርቅ ምርት 513 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል

173

ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት 11 ወራት ከወርቅ ምርት 513 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የተቋሙን የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ከወርቅ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው ምርት ነው።

የወጪ ንግድ ማዕድናትን በስፋት፣ በጥራት እንዲሁም በአይነት እንዲመረቱ በማድረግ የዘርፉን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የተለያዩ የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በገቡት የውል ስምምነት መሰረት ያልሰሩ የተለያዩ ኩባንያዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ የጠቆሙት ኢንጂነር ታከለ፤ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ ወስደው ስራዎቻቸውን ያላከናወኑ 116 የማዕድን ምርመራ ፈቃዶች መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም የተለያዩ የማዕድናት ምርት ፈቃድ ወስደው ስራቸውን ያላከናወኑ ስድስት የማዕድን ፈቃዶች መሰረዛቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ባደረገው ክትትል 850 የሚሆኑ ማዕድን ላኪዎች ፈቃዳቸውን ሽፋን አድርገው ህገ-ወጥ ስራ ሲያከናወኑ በመገኘታቸው የተሰጣቸው ፈቃድ እንዲሰረዝ መደረጉን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ውላቸውን ያላከበሩ 972 ባለፈቃዶች ፈቃዳቸው መሰረዙን ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገወጥ ድርጊቶች ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም