የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታት ከአለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ላይ የ35 በመቶ ጭማሪ ተድርጎ ግዢ ይፈጸማል-ብሔራዊ ባንክ

68

ሰኔ 25ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታት ከአለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ላይ የ35 በመቶ ጭማሪ አድርጎ ለመግዛት መወሰኑን አስታወቀ።

የባንኩ የከረንሲ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አበበ ሰንበቴ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታትና የኮንትሮባንድ ንግዱን ለመቆጣጠር ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከአለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ላይ እንደ ወርቁ ብዛት ከአስር በመቶ እስከ 29 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ይገዛ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የወርቅ አቅርቦት መገኘቱን አስታውሰዋል።

በእነዚህ ዓመታት ባንኩ ከወርቅ ግብይት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አግኝቷል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚመጣው የወርቅ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ አምራቾችን ለማበረታታት ለሁሉም ወርቅ አቅራቢዎች እኩል በ35 በመቶ ጭማሪ ግዥ ይፈጸማል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም