የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር የምስራቅ አፍሪካና የዓባይ ተፋሰስ አገራት ሊደግፉትና ሊያስቀጥሉት ይገባል

103

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር የምስራቅ አፍሪካና የዓባይ ተፋሰስ አገራት ሊደግፉት ይገባል ሲሉ በጉለሌ እጽዋት ማዕከል የእጽዋት ተመራማሪና ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ በላይ ገለጹ።

ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የአገራችንን ብሎም የቀጣናውን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው ብለዋል።

ደን ዝናብ በመሳብና ውሃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ በማድረግ የትነት መቀነሻ መሳሪያ በመሆን እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

በተጨማሪም የደረቁ ወንዞችና ምንጮች ውሀ እንዲያመነጩ ለማድረግና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አብራርተዋል።

በተለይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ለአረንጓዴ አሻራ በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው ከኃያላን አገራት የካርበን ልቀት ጋር ተዳምሮ ለተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እንደዳረጋቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራትም ጭምር ችግኞችን የምታቀርበው ከችግሩ በጋራ ለመላቀቅ በማሰብ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር የቀጣናው አገራት ሊደግፉትና ሊያስቀጥሉት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ወንዞች ውሃ በብዛት የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ተራሮች ከሚገኘው ደን መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ተራሮችና ደኖች ለታችኛው ተፋሰስ አገራት የውሃ መሰረቶች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ለደን ልማት ትኩረት በመስጠት አንገብጋቢ የሆነው የውሃ ፍሰት ጉዳይ ከተጠበቀ ደግሞ በአገራት መካከል ግጭት እንዳይኖር ያስችላል ነው ያሉት።

ስለዚህ አረንጓዴ አሻራ በቂ ውሀ ወደታችኞቹ ተፋሰስ አገራት እንዲደርስና በደለል እንዳይጠቁ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ አገራቱ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ባለፉት ሦስት ዓመታት 18 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር   7 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን 52 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም