የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው--የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት

106

ሰኔ 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ተናገሩ።

አራተኛው ዙር አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጉለሌ እጽዋት ማዕከል በይፋ የተጀመረ ሲሆን ፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት በመርሃ-ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ችግኝ መትከል በተለይ ለአፍሪካ መልከ-ብዙ ፋይዳ አለው፡፡

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ተደጋጋሚ ድርቅ እያጋጠማት መሆኑን ጠቅሰው፤ አህጉሪቷን ከዚህ ችግር ለማውጣት እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ የደን ልማት ንቅናቄዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ላስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና መርሃ ግብሩ እውን እንዲሆን እየተሳተፉ ለሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ሊቀመንበሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም መስፋፋት እንዳለበት ገልፀው፤ በተለይም በበርሓማነት መስፋፋትና በድርቅ ክፉኛ ለተፈተነው የአፍሪካ ቀንድ አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ሌሎች የአፍሪካ አገራትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአርያነት ሊወስዱት እንደሚገባም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ጨምሮ ለሌሎች የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም