የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ስኬት ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ታላላቅ የልማት ውጥኖች እውን እንደምታደርግ የሚያመላክት ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

144

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ታላላቅ የልማት ውጥኖች እውን እንደምታደርግ የሚያመላክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በጋራ እንደተሳተፍን ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላትን በትብብር ማጥፋት አለብንም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 4ኛውን አገር-አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን በጉለሌ እጽዋት ማዕከል በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

በመርሐ-ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ ማሃመት፣ የክልል ርእሳነ-መስተዳድሮች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ጋር በማስታረቅ ሃብታችንን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ባለፉት ሶሰት ዓመታት 18 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው ይህ ውጤት ታላላቅ የልማት ውጥኖችን ለማሳካት ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ የልማት ስራዎችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በሚገባ ማጠናቀቅ እንደምትችል ያመለከተ ስለመሆኑም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ማደስ አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ መንግስት ለሀገር ልማት የማይበጁ አሮጌ አካሄዶችን በማሻሻል ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ሁሉም በመሳተፍ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ሃብት ማደስ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ ታላቅ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያ በታደሰ አእምሮ ለማገልገል መነሳት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአረንጓዴ አሻራ ልማት እያደረግን ያለው ትብብር የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ጠላቶችን ለማጥፋት መድገም አለብን ነው ያሉት፡፡

የጸጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለዜጎቿ እንዳትመች ለማድረግ የሚሰሩ የጠላት ተላላኪ አካላት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ አመራሩ ይህንን ተግባር ሊደግፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን፤ ባለፉት ሶስት አመታት 18 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው የጽድቀት መጠናቸውም ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተዘጋጁት ችግኞች 52 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በየዓመቱ በአማካኝ 20 ሚሊዮን ዜጎች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ መርሃ ግብሩ በየዓመቱ ከ184 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም