በክልሉ ጠረፋማ አከባቢዎች የሚፈጸሙ ህገወጥ ንግዶችን ለመከላከል የአከባቢውን ህብረተሰብ ያሳተፈ ስራ መሰራት አለበተ--ነዋሪዎች

98

ጂጂጋ ሰኔ 14/2014 (ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ጠረፋማ አከባቢዎች የሚፈጸሙ ህገወጥ ንግዶችን ለመከላከል የአከባቢውን ህብረተሰበ ያሳተፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

ህግ ወጥ ንግድን ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ሱልጣን አብዲ አሊ እንዳሉት በጠረፍ አከባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ የህገወጥ ንግድ በሀገር እድገትና ሰላም ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ መሠረታዊ ሸቀጦችን በህጋዊ መንገድ እንዲያገኙ የሚያስችለውን የጠረፍ ንግድ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።

በጠረፋማ አከባቢዎች የሚኖረው ህብረተሰቡ በህገወጥ ንግድ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲይዝ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ሱልጣን የተናገሩት።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሱልጣን ዶዲ አርብቶ አደሩ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የቤት እንስሳቶቹ ህገወጥ ናቸው እየተባለ በጉምሩም ኮሚሽን ሰራተኞች እንደሚያዙባቸው  ተናግረዋል።

ህግ ወጥ ንግድን በመከላከል ስራው ላይ ህብረተሰቡ ባለቤት እንዲሳተፍ በማድረግ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ ነው የጠየቁት።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከአጎራባች ጂቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ሀገራት ጋር የጠረፍ ንግድ ስምምነት እንዳላት ገልጸው፤ ከሱማሊያና  ከኬንያ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለመፈፀም  በሄደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የቁም እንስሳት ንግድ ህግ መኖሩንም ጠቅሰው የገቢና ውጪ ህገወጥ ንግድን ከመሰረቱ ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ መሰራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንዳሉት ኮሚሽኑ "ከለውጡ በፊት የነበሩ አመራሮች ተቋሙን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሳይሆን የአንድ አከባቢ ስዎች ማዕከል አድርጎ የቆዩትን ሁኔታ የመቀየር ስራ አከናውኗል።"

በቅርቡ የሶማሌ ክልል ተወላጆችን ጨምሮ መልካም ስነ ምግባር ያላቸውን ተጨማሪ 1 ሺህ ሰዎች ለመመልመል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሀመድ በበኩላቸው ህገወጥ ንግድ  በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተግባሩን በመከላከል የህዝቡ ሰላምና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ ለማሻሻል የሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ ከፌደራልና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም