ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያስችል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

125

አዳማ፣ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያስችል ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ።

ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት እስካሁን የተከናወኑ ስራዎችን የሚገመግም ዓለምአቀፍ የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው እንደገለፁት፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ዘርፈ ብዙ መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየሆኑ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭነት መንስኤ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቁ ሙቀት አማቂ በካይ ጋዞች የተነሳ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ የምግብ እጥረትና ራስን በምግብ ያለመቻል ችግሮች እየተከሰቱ እንደሆነ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቷን ተናግረዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ፣ በአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ በታዳሽ ሃይል ልማትና አቅርቦት ላይ የተሰሩ ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጫናን ለመቋቋም ማገዙን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን በዘላቂነት ለመቀልበስ የቀጣይ አስር ዓመት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ ፎኖተ ካርታና የዘርፉ የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉም ሴክተሮች የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይን በዕቅዳቸው አካተው እንዲተገበሩ በማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ሙቀት አማቂ ጋዞችን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ዕድገት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት በአረአያነት እንደምትጠቀስ ጠቁመዋል።

ሙቀት አማቂ ጋዞች ተፅዕኖን ለመቀነስ የሚያስችል የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንዲዘጋጅና እንዲተገበር እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለመደው አካሄድ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታን የዳሰሱ ጥናቶችና የግምገማ ሞዴሎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

በተለይ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪዎችና መሰል ተቋማት ጥናቶች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል።

የረዥም ጊዜ የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ ስትራቴጂ በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ ስናስብ በአረንጓዴ አሻራ፣ በአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ በደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ በመሆናቸውን ገልጸዋል።ለስትራቴጂው ውጤታማነት ቁልፍ መሳሪያ እንደሆኑም አስረድተዋል።

ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ ቁልፍ ስራችን ዛፎችን በስፋት መትከል ነው ያሉት ዶክተር ገመዶ፤ ኢትዮጵያ የምትተገብረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ከስትራቴጂው ጋር ተመጋጋቢ ናቸው ብለዋል ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም