በተደጋጋሚ እርሻ የቀነሰውን የመሬት ለምነት ለመመለስ ዛፎችን መትከል ይገባል

95

ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ለዘመናት በቆየው ተደጋጋሚ እርሻ የቀነሰውን የመሬት ለምነት ለመመለስ ዛፎችን በመትከል አፈሩን ማደስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 4ኛውን አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያዊን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን ሲተክሉና አምስት ሺህ ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት የሚችለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲገነቡ የማንንም ድጋፍና እርዳታ አልፈለጉም ብለዋል፡፡

ይሄውም ለምናስበውና ለምንተልመው የኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በአረንጓዴ አሻረ መርሃ ግብሩ ለምግብነት የሚያገለግሉ፣ ለመድሃኒትነት የሚውሉ፣ አካባቢን የሚያክሙና ተፈጥሮን የሚያስውቡ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እርሻን ቀድማ የጀመረች ቀደምት አገር በመሆኗ በተደጋጋሚ እርሻ ለምነቱን ያጣው መሬት የተሻለ ምርት ይሰጥ ዘንድ ዛፎችን በመትከል አፈሩን ማደስ ይገባል ብለዋል፡፡

"በአሮጌ አስተሳሰብና አተያይ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ስለማይቻል ህጎችና አሰራሮች እየተሻሻሉ እንዳሉት ሁሉ በአሮጌ ሰፈርና በአሮጌ ቤቶች ምድርን ማደስ አይቻልም" ብለዋል፡፡

በአንድ ሄክታር ላይ ያለን ዛፍ 14 ሺህ ኪሎ የተነዳን መኪና የተቃጠለ አየር እንደሚሰበስብ ጠቅስው በኢትዮጵያ ካለው የሚኪና ቁጥር አንፃር የከባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል በርካታ ችግኞችን መትከል ይገባልም ነው ያሉት።

የብልጽግና መሰረት ከምንጥላባቸው መንገዶች አንዱ ዛፍ መትከል በመሆኑ ሁሉም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሁለት ወር ውስጥ ቢያንስ 100 ችግኞችን በመትከል አርዓያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በዓለም ላይ ከ60 ሺህ ባልበለጡ የዛፍ ዝርያዎች ከሶስት ትሪሊዬን በላይ እዕዋት እንዳሉት ሁሉ እስከ ሰባት ሺህ የሚደርስ ሀገር በቀል ዛፍ ያላት ኢትዮጵያ 20 ቢሊዬን ችግኝ ብትተክል ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም ብለዋል።

እውቀትና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ፣ የአገራችንን እምቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀምና ሀገራችንን መንከባከብ ወደ ብልጽግና መንገድ ይመራናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ሆኖም ችግኝ መትከል እንደሚቻል ለማሳየት በዘርና በሀይማኖት በመከፋፈል ንጹሃንን በመጨፍጨፍ ሰው በነፃነት መኖር የማይችልባት ምድር ለማድረግ የሚሰሩ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ ይገባልም ብለዋል፡፡

በእነዚህ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ሃይሎች ላይ የመከላከያ ሰራዊት ከትናንት ጀምሮ ጠንካራ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የሚጠበቅባቸውን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም