የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል - የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር

105

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እና የዕድገት ጉዞ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር አስታወቁ።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር የስራ ሀላፊዎች  በነዳጅ ድጎማ ስርዓት ምንነትና አተገባበር ላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ከድር ጁሃር እና ካቢኔ አባላት ጋር ትላንት ተወያይተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ለአገር ብልፅግናና ቀጣይነት ያለው ዕድገት አበርክቶው የጎላ ነው።

"ስለ አዲሱ አሠራር በየደረጃው ለሚመለከተው አካላት በማስረዳት ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ይሰራል " ያሉት ከንቲባው በተለይም ህገወጥ የነዳጅ ዝውውርን በመከላከል እረገድ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በአዲሱ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርአት ለድሬዳዋ የሚቀርበው የነዳጅ መጠን ከከተማው ዕድገት ጋር የተጣጣመ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለከተማው የተመደበ የነዳጅ ኮታና ከተማው እያስተናገደ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥር የማይመጣጠን መሆኑን ጠቁመው በተለይም በጁቡቲ መስመር የሚጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የሚቀዱት ለከተማው ከሚቀርብ ኮታ በመሆኑ በአዲሱ አሰራር ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው "በነዳጅ ዋጋ ላይ የተካሄደው የለውጥ አሰራር ከአሁን በፊት በጅምላ ሲደረግ የነበረውን አካሄድ የሚለውጥና የአገሪቱን የዕዳ ጫና የሚያስቀር ይሆናል" ብለዋል።

ሀገሪቱ ስትከተል በነበረው የነዳጅ ድጎማ ለ132 ቢሊዮን ብር እዳ መዳረጓን ጠቁመው ድጎማው ኢ- ፍትሀዊ፣ ደሀውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያላደፈረገ፣ ኮንትሮባንድን የሚያበረታታና   በሁሉም መስክ የሀገሪቱን እድገት ያጓተተ እንደነበር ጠቁመዋል።

የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ በማድረግ ደሃውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የታለመ የነዳጅ ድጎማ አፈፃፀም ስርዓት /ሪፎርም/ መዘርጋቱን ጠቁመው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ከሚቀጥለው በጀት አመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርአት ከነዳጅ አቅርቦት እና ግብይት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሄ እንደሚያመጣ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም