በቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል በስንዴ ምርት ምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው

70

ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን በማዕከሉ የዱረም ስንዴ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ገለጹ።

ማዕከሉ በአገር ውስጥ የስንዴ ምርት ለማሳደግ ከሚያደርገው ምርምር በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ስንዴ በማስገባት የማዳቀል ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑም ታውቋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ለዳቦ፣ ለፓስታና ማካሮኒ የምርት ግብዓት የሚሆኑ የዱረም ስንዴ ምርት በስፋት በመመረት ላይ ይገኛል።  

በቢሾፍቱ በሚገኘው ግብርና ምርምር ማዕከል የዱረም ስንዴ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ሽታዬ ሆማ፤ ማዕከሉ በምርምር የተሻለ ምርት የሚያስገኙ የስንዴ ዝርያዎችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ጥራት ያላቸውና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን በማውጣት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከምርምር ሥራው ባለፈ የዱረም ስንዴ ለፋብሪካ በሚሆን መልኩ ደረጃውን ጠብቆ እንዲመረት ለማድረግም እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑን ዶክተር ሽታዬ ተናግረዋል።

ከአርሶ አደሮች ማሳ ከሚሰበሰበው የስንዴ ምርት ከሚያደርገው ምርምር በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ስንዴ በማስገባት የማዳቀል ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር ንብረት እና የአፈር አይነት የሚስማማው የስንዴ ዝርያ በመፍጠር ለምርታማነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

ማዕከላቸው በዱረም ስንዴ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ምርምር እያደረገ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ቢሆንም አርሶ አደሮች የገበያ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋብሪካዎች ለፓስታና ማካሮኒ ምርት ግብዓት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በመጠቀማቸው ለዱረም ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች ገበያ ማጣት ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በማዕከሉ በኩል አርሶ አደሮችን እና ፋብሪካዎችን ለማስተሳሰር ቢጥርም ውጤቱ የሚፈለገውን ያክል አይደለም ብለዋል፡፡

መንግሥት የስንዴ ምርት ከውጭ ላለማስገባት እየሄደበት ያለው እርቀት በተለይ ፋብሪካዎች አገር ውስጥ የዱረም ስንዴ ምርትን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ በመሆኑ ችግሩን ሊፈታው እንደሚችል ገልጸዋል።

በማዕከሉ የእጽዋት ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ ዘመዴ፤ መንግሥት ለስንዴ ምርት የሰጠውን ትኩረት ለማሳካት ማዕከሉ ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በበጋ ወራት በመስኖ እና በክረምት ወራት ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት የስንዴ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገውን እቅድ ለማሳካት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከሉ ምርምር የተገኘው የዱረም ስንዴ የፋብሪካዎችን የጥራት ደረጃ ማሟላት የሚችል መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም