ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች ጋር ተወያዩ

86

ሰኔ 14 ቀን 2014(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ዙርያ ያሉ ሁኔታዎችን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላላት አጋርነት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ እና ከኮሚሽኑ እና ከአባል ሀገራቱ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት በተመለከተም ለትግራይ ክልል የሚደርሰው ዕርዳታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንት 500 የጭነት መኪኖች ከያዘው ግብ ባለፈ የማድረስ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

አጋር አካላት የአማራ እና አፋር ክልሎችምንም ጨምሮ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑ ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ስላላቸው ወሳኝ እርምጃዎች እና ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር በሚመለከት ለኮሚሽነሩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በአፍሪካ ህብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኩል እየተደረጉ ያሉ የሰላም ጥረቶች ላይ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋቸዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሰላም ውጥኖች ላይ ህወሓት ያሳየውን አሳማኝ ያልሆነ የመጠራጠር አቋምንም ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው መንግስት በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያቀርቡ አጋሮች ተጨማሪ ነዳጅ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ሌሎችም ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲሄዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁለቱ አካላት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት ጊዜ በተከሰቱት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተጠያቂነት እርምጃ፣ ይህንን የሚያረጋግጥ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በማቋቋም እና በሰብአዊ መብት አያያዝ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ላይ ስላሉ ጉዳዮችም ተወያይተዋል።

ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩም ህብረቱ ለሰላም ሂደቱ ያለውን ድጋፍ ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ኮሚሽነሩ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ስለሚሹ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ጉዳይም ምክክር አድርገዋል።

የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታቸው በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ጉዳት በአካል ለማየት የሄዱ ሲሆን በትግራይ ክልልም የሰብዓዊ ሁኔታን ይገመግማሉ።

1010

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም