የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤት ታላላቅ የልማት ውጥኖችን ለማሳካት ትምህርት የሰጠ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

189

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጋራ እንደተሳተፍን ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ጠላቶችን በትብብር ማጥፋት አለብን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 4ኛውን አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዛሬው እለት አስጀምረዋል።

በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክትም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ታላላቅ የልማት ውጥኖችን ለማሳካት ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ጋር በማስታረቅ ሃብታችንን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሶሰት ዓመታት 18 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን አስታውሰው፤ ውጤቱ ታላላቅ የልማት ውጥኖችን ለማሳካት ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም በመሳተፍ ኢትዮጵያን ለማደስ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ እንተባበር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ልማት እያደረግን ያለው ትብብር የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ጠላቶችን ለማጥፋትም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ እንደሚገኙባቸው ጠቁመዋል።

ባለፉት ሶስት አመታት 18 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው የጽድቀት መጠናቸውም ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን አስታውሰው፤ የመሬት መራቆትን ለመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከልና የምግብ ዋስናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊዮን ችግኝን ለመትከል ታቅዶ በቂ ችግኞች መዘጋጀታቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም