የውጭ አገራት ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚተገበር የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው

104

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውጭ አገራት ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚተገበር የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ አገራት ክፍት ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ይገኛል።

በመሆኑም ዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን በተወሰኑ ተዋናዮች ብቻ ታጥሮ የቆየው የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በዚህም መሰረት ባንኮቹ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ዘርፉ የሚመራበት የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው ለኢዜአ ገልጸዋል።

የባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት ለእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን ለመጨመር፣ የብድር አገልግሎትን ለማስፋትና ሌሎችም ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ በፋይናንስ መደገፍና አዳዲስ አሰራሮችን ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።

የባንኮቹ ወደ አገር ውስጥ መግባት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ በሂደቱ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋት ሊቀንስ የሚችል የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገር ውሰጥ ባንኮች ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሰው ኃይል፣ በአቅም እና በቴክኖሎጂ ጭምር በመጎልበት  ለውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

የተጠናከረና የተደራጀ ባንክ ከመፍጠር አንጻር በራሳቸው ፈቃድ አንዱ ከሌላው ጋር የመዋሃድ አማራጭን መከተልም ወሳኝ መሆኑን መክረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የህግ ማዕቀፉ በሚፈልገው ልክ ጠንካራ፣ ብቁና አስፈላጊውን መስፈርት የማያሟሉ ባንኮች ካጋጠሙ በመዋሃድ መሥራት በአማራጭነት የሚወሰድ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም