የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራምን ለማሳካት ከውጪ አገራት በጎ ፈቃደኛ መምህራንን የማሳተፍ ስራ ተጀምሯል

66

ሰኔ 13/2014 (ኢዜአ) የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራምን ለማሳካት ከውጪ አገራት በጎ ፈቃደኛ መምህራንን የማሳተፍ ስራ መጀመሩን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብለት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በትምህርት ዘርፉ ላይ እየተደረጉ ባሉ ለውጦች ዙሪያ እና በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ መክረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል እና መሰረት ለመጣል የሚረዱ የሪፎርም ስራዎች በትምህርት ዘርፉ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራምን በተመለከተ የበጎ ፈቃደኛ መምህራንን በብዛት ለማስመጣት ስራዎች መጀመራቸውን እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል ።

ከአውስትራሊያም ከ1ሺህ ያላነሱ የበጎ ፈቃድ እንግሊዝኛ መምህራን እንደሚፈልጉም ለአምባሳደሯ ገልፀውላቸዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት በበኩላቸው÷በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሪፎርም እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።

በአውስትራሊያ 16 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ መኖሩን ጠቅሰው÷ እነዚህን እና አውስትራሊያውያንን በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም