የሶስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

143

ሰኔ 13/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ 3ኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የከተማዋ ጤና ቢሮ አሰታወቀ።

ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና በጊዜያዊነት በተቋቋሙ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል።

መርኃ ግብሩ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሚኪሌላንድ ጤና ጣቢያ የቢሮው ሃላፊዎች ፣የጤና ባለሙያዎችና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በመከላከል ሂደት እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በ2013 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ መጀመሩን አስታውሰው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ባይቻልም ቅደም ተከተል በማስቀመጥ ክትባቱን መስጠት መቻሉን አስታውሰዋል።

የክትባቱ አቅርቦት እየተሻሻለ ከመጣ በኋላ ግን በ2ኛው ዙር ዘመቻ ላይ ለበርካቶች ተደራሽ ለማድረግ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ደግሞ ሶስተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ዘመቻው በይፋ ተጀምሯል ብለዋል።

ለክትባት ዘመቻው ከ250 በላይ የህክምና ቡድኖች እና ከ249 ሺህ በላይ የክትባት ዶዝ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በዘመቻው እድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሚከተቡ ጠቁመው ቀደም ሲል አንደኛውን ወስደው ሁለተኛውን ያልወሰዱም መከተብ ይችላሉ ብለዋል።

በተጨማሪም የማጠናከሪያ ክትባት (BUSTER DOZZ) ለመውሰድ ጊዜያቸው የደረሰ ዜጎች መከተብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በ3ኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ከ70 እስከ 80 በመቶ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱንም ዶክተር ዮሃንስ ገልጸዋል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽ እያገረሸና እየተሰፋፋ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው የከተማዋ ነዋሪዎች ይህንን መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙ አንደሚገባ አሳስበዋል።

ክትባቱን የወሰዱት አቶ ፍቃዱ ሁሴን በሰጡት አሰተያየት ኮቪድ-19 አሁን ላይ እየተባባሰ መምጣቱን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም የኮቪድ-19 መርሆችን መጠቀም እና ክትባቱን መከተብ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ማህበረሰቡ በነጻ የተዘጋጀለትን ክትባት መውሰድ ይገባዋል ሲሉ ይመክራሉ።

የስኳርና የደም ግፊት ህመምተኛ በመሆናቸው ከተላላፊ በሽታዎች ለመጠበቅ ሲሉ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንደወሰዱ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ መስፍን ናቸው

በከተማ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ክትባት ተደራሽ ሆኖ 822 ሺህ 636 ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ክትባቱን ያጠናቀቁ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም