አሸባሪዎችንና ጽንፈኞችን ለህግ የማቅረቡ ስራና ተጎጂ ቤተሰቦችን መልሶ የማቋቋሙ ተግባር በትኩረት ይሰራል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

95

ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪዎችንና ጽንፈኞችን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ተጎጂ ቤተሰቦችን መልሶ የማቋቋሙ ተግባር በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን "አሸባሪ ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ በፈፀመው ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ" ሲሉ የሐዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።'

በፀጥታ አስከባሪ አካላትና በህዝቡ የተባበረ እርምጃ በአሸባሪውና ፅንፈኛው ቡድን ላይ በደረሰበት ሽንፈትና ኪሳራ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎችን በአፀፋው እየወሰደ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን አሸባሪው ቡድን በቅርብ ጊዜ በጋምቤላ አካባቢ ያደረገው ሙከራ ሲከሽፍበት በምዕራብ ወለጋ በጊምቢ አካባቢ ደግሞ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተለይም በህጻናትና በሴቶች ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ እና ኢሰብዓዊ ነው ያሉት፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኑ በወሰደው እኩይ የጥፋት እርምጃ ምክንያት በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ጉዳትም የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ህግ የማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ተጎጂ ቤተሰቦችን የማረጋጋት፣ የመደገፍ እና መልሶ የማቋቋም ስራ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፤አሸባሪዎችን እና ጽንፈኞችን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም