የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የተነሳባቸው ከ100 በላይ አቤቱታዎች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል

205

ሰኔ 13/2014/ኢዜአ/ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላስነሱ ከ100 በላይ አቤቱታዎች ውሳኔ መሰጠቱን የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ገለጸ።

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን ያለው ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

ተቋሙ በፌዴራል መንግስትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ህጎች ከሕገ መንግስቱ ጋር ይቃረናሉ የሚልና በፍርድ ቤቶች የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሲነሳ በማጣራት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡

በአጣሪ ጉባኤው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ የቀረቡ ጉዳዮችን በተመለከተ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወዬሳ፤ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ባለፉት 14 ዓመታት የህገ መንግስት ትርጉም ይሻሉ ተብለው ከቀረቡት ከ7 ሺህ በላይ አቤቱታዎች በርካቶቹ የግለሰብ አቤቱታዎች ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ የሕገ መንግስት ጥሰት የተፈጸመባቸው ጉዳዮች ናቸው በሚል የተለዩ 102 የሕገ ጉዳዮች ተለይተው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው አብዛኛዎቹ አከራካሪና ውስብስብ ሲሆኑ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ታይተው የመጡ ናቸው ብለዋል።

በተለይም ሕጎችን አስመልክቶ ሕገ መንግስቱን በመጥቀስ የሚነሱ አቤቱታዎችን በተመለከተ ጉባኤው አጣርቶ ውሳኔ እንደተሰጠበትም ገልጸዋል።

በጽሕፈት ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ሙሉዬ ወለላው፤ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ካስነሱ አቤቱታዎች ጥቂቶቹን ዘርዝረዋል።

የፍትሕ መከበርና የእኩልነት መብት፣ የንብረት ያለአግባብ መወሰድ፣ የሴቶችና ህጻናት መብት ጥሰት ከሚጠቀሱት ማካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክትትል ማነስ፣ የባለሙያዎች እጥረትና አቤቱታ የሚቀርብበት አካባቢ መራቅ ለውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመሆን ቸግር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በህብረተሰቡ በኩል ምክር ቤቱን ወይም አጣሪ ጉባኤውን እንደ አንድ ይግባኝ ሰሚ አካል አድርጐ የመመልከት ችግርም መኖሩን ጠቅሰዋል።

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ 11 አባላት ያሉት ሲሆን ከአባላቱ መካከል ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች እንዲሆኑ በሕገ መንግስቱ ተደንግጓል።

አጣሪ ጉባኤውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት በቅደም ተከተል በሰብሳቢነትና ምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም