የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት የዘመኑ ትልቅ ፈተና ናቸው - አባላቱ

101

አዳማ ሰኔ 12/2014(ኢዜአ)... የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት የዘመኑ ትልቅ ፈተና ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት ገለፁ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የቦርድ አመራር አባል የሸዋ ማስረሻ እንደገለፀችው የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች "የዘመናችን ትልቁ ፈተናዎች ናቸው"።

ይህም ቴክኖሎጂው የወለዳቸው መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ያለመጠቀም የፈጠረው ክፍተት መሆኑንም ገልፃለች።

ሐሰተኛ መረጃዎችን በተለይ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ ፎቶዎች፣ የድምፅ ቅጂዎችና የፅሑፍ መልዕክቶችን ሳይቀር እውነታውን ወደ ጎን በመተው አመሳስሎ ወደ ህብረተሰቡ የማሰራጨት ተግባር በከፍተኛ ደረጃ መበራከቱን ተናግራለች።

መሰል ድርጊቶች ደግሞ ለጋዜጠኞች ፈተና መሆናቸውን ጠቅሳ፤ በተለይ የሚዲያ ባለሙያዎች እውነተኛ መረጃ ከማግኘትና ከማጥራት እንፃር የተሻለ እድል ያላቸው ቢሆንም ተጋላጭነቱ አለ ብላለች።

ማህበራዊ ሚዲያን እንደ ምንጭ የሚጠቀሙ መኖራቸውን የገለጸችው ጋዜጠኛ የሸዋ፤ አሳሳች ገፆች እየተከፈቱ ተጋላጭነቱ እየጨመረ በመሆኑ በሁሉም ላይ ተፅዕኖው እየጎላ መምጣቱን ገልጻለች።

በመሆኑም መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመዋጋት የተደራጀ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግራለች።

በማህበራዊና መደበኛ የሚዲያ አውታሮች ላይ የሚዘዋወሩ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን እየተከታተልንና እያጣራን ለህዝቡ እያቀረብን ነው ያለችው ደግሞ የሃቅ ቼክ የመረጃ አጣሪ ድርጅት ተወካይና አሰልጣኝ ሪሆቦት አያሌው ናት።

ህብረተሰቡ ስለ ሐሰተኛ መረጃ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና እንዲያጤነው እየሰራን ነው ያለችው ተወካይዋ፤ በዚህም የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን እየተዋጋን ነው ብላለች ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ርብቃ ታደሰ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን መዋጋት ወቅታዊና እጅጉን አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተለይ ሴት የሚዲያ ባለሙያዎች የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመታገል በዘርፉ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ራሳቸውም ከእንደዚህ አይነት መረጃ ስርጭት እንዲቆጠቡ ጭምር በአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች ራሳቸው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎች ሰለባ ሲሆኑ እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው፤ ዋናው የሚዲያ ስነ ምግባርና የዘርፉን የህግ ማዕቀፎች ተከትሎ እንዲሰሩ ጥረት ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የህግ አገልግሎትና የቅሬታ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ቆንጂት ታምራት በበኩላቸው ባለስልጣኑ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና አካላት በተቀመጠው የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች መሰረት እየሰሩ መሆኑን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭቱን ጨምሮ የሞኒተሪንግ ስራ እየሰሩ ጋዜጠኞች ችግሩን ለመቋቋምና ለመዋጋት በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ግንዛቤ አግኝተው የድርሻቸውን እንዲወጡ በአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

በመገናኛ ብዙሃንና የዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።

ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ህግን ሽፋን በማድረግ ማሰራጨት እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት ለሁለት ቀናት በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ላይ በአዳማ ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም