የደሴ ከተማ አስተዳደር በአንድነት ወደ ሰላምና ልማት መግባቱን አስታወቀ

275

ደሴ ኢዜአ ሰኔ 12/2014… “አሸባሪው ህወሓት ካደረሰብን የስነ ልቦና ጫናና ቁዘማ ወጥተን በአንድነት ወደ ሰላምና ልማት ዙረናል” ሲሉ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር 8ኛው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፌስቲቫል  በደሴ ዛሬ ተካሂዷል ።

አሸባሪው ህወሃት ከፈፀመው የንብረት ዘረፋና ውድመት ባለፈ ያደረሰው ሰብዓዊ የመብት ጥሰት የህብረተሰቡን ስነልቦና በመጉዳቱ እንዲቆዝም አድርጎት እንደነበር አቶ ሳሙኤል በዚሁ ጊዜ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ውድመቱን መልሰው በቅንጅት እያቋቋሙ የህብረተሰቡን ስነልቦና ለመገንባት የተለያዩ ስልጠናዎችም መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል አክለውም “በመሆኑም አንድነታችንን ጠብቀን በሙሉ ቀልባችን ወደ ልማትና ሰላም ዙረናል” ብለዋል።

በሽብር ቡድኑ ስራቸው ተቋርጦ የነበሩ መሰረተ ልማት ስራዎች መልሰው ተጀምረው እየተፋጠኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡም ተረጋግቶ የእለት ተዕለት ስራውን በነፃነት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰይድ አራጋው በበኩላቸው ስፖርት ልማትንና አንድነትን ለማጠናከር አይነተኛ ሚና አለው።

“የዛሬው የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙታችንን ለማጠናከር ያግዘናል” ብለዋል።

በተለይ ከአማራ ክልል ሁሉም ዞኖችና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የስፖርት ቤተሰቦች መሳተፋቸው የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

ከፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ቃል ኪዳን ፍሬው በሰጠችው አስተያየት ከአሸባሪው ህውሓት ሁለተናዊ ውድመትና ጥቃት በኋላ ወደ ሰላምና ልማት መመለሳቸውን አስደስቷታል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች እየተሳተፍን የእርስ በርስ ግንኙነታችንን እያጠናከርን፣ ልማቱንም እየደገፍን ነው ብላለች።

ከአሸባሪው ህውሃት ውድመት በኋላ የደሴ ከተማ ሁለተናዊ እንቅስቃሴ በፍጥነት እዚህ መድረሱ በጣም አስገርሞኛል፣ አስደስቶኛልም ያለው ደግም ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጣው ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ደበበ ነው።

በተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን በማጠናከር ኢትዮጵያን እንጠብቃለን ብሏል።

በፌስቲቫሉ ከአማራ ክልልና ሌሎች ክልሎች የተውጣጡ አመራሮች፣ የስፖርት ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።