በክረምቱ ለጤና እክል የሚሆኑ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል የህብረተሰቡ ጥንቃቄ ወሳኝ ነው

91

ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)በክረምቱ ለጤና እክል የሚሆኑ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል የህብረተሰቡ ጥንቃቄ ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በዝናብ ወቅት በጎርፍና ተያያዥ መንስኤዎች ለማህበረሰብ ጤና ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶችን በሚመለከት ኢዜአ ከጤና ሚኒስቴር የሃይጅንና የጤና አጠባበቅ ምክትል ዳይሬክተር አሽረፈዲን ዮያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በክረምት የዝናብ መብዛትን ምክንያት በማድረግ በሚታቆር ውሃና ጎርፍ በተለምዶ የውሃ ወለድ በሽታ የመከሰት አጋጣሚው የበዛ ነው ብለዋል።

የውሃ ወለድ በሽታ ዋነኛ ምክንያቱ የውሃ ብክለት መሆኑን ጠቁመው በተለይም ኮሌራ፣ተቅማጥ እንዲሁም የቆዳ እና ተያያዥ የጤና ችግሮችን የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።

የበሽታውን ምክንያት በቅጡ በመረዳት ህብረተሰቡ ተገቢውን የመከላከል ስራ እንዲያከናውን ሚኒስቴሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ይሄው ተግባር ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።

የውሃ እና የምግብ ብክለትን መከላከል በሚቻልባቸው ዘዴዎች ላይ በማተኮርም ከመከላከል አንፃር ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር በመተባበር ብዙ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግስትና እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር የማህበረሰብ ጤናን የመጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተበከለ ውሃ እና አጠቃላይ የንፅህና መጓደል ምክንያት ከኮሌራና ተቅማጥ በተጨማሪ ሄፓታይተስ ኤ፣ታይፎይድ፣ፖሊዮ እና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች የሚያስከትል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኮሌራ በሽታ እ.ኤ.አ ከ2000 እሰከ 2015 ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከ80 በመቶ በላይ የሞት መንስኤ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም