የአማራና የአፋር ክልል ህዝቦችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መድረክ በኮምቦልቻ እየተካሄደ ነው

73

ሰኔ 12 ቀን 2014(ኢዜአ)የአማራና የአፋር ክልል ህዝቦችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የአማራ ክልልሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በመድረኩ ላይ እንደገለፁት አሸባሪው ህውሃት ሁለቱን ክልሎች ለማጋጨት ባለፉት 27 ዓመታት በሴራ ፖለቲካ ሲሰራ ቆይቷል።

የሽብር ቡድኑ ያለመው የጥፋት ጉዞው ካለመሳካቱ ባለፈ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሴረውን ሴራ መላ ኢትዮጵያውያን በመረባረብ ማክሸፍ መቻላቸውን ገልፀዋል።

አልፎ አልፎ በግጦሽ፣በእርሻ፣በእንሰሳት ስርቆትና በሌሎችም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በባህላዊ ግጭት አፈታት ዘዴ በመፍታት ህብረተሰቡን በልማት ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩም ''ግጭትና ኮሚውኒኬሽን'' በሚል ርዕሰ በምሁራን ጥናት እየቀረበ ሲሆን በቀረበው ጥናት ዙሪያ ውይይት በማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ከሁሉቱም ክልሎች የተውጣጡ አመራሮች፣የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም