ህዝብን ለማገልገል የገባነውን ቃል በተግባር ለማስቀጠል የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል

61

ሰኔ 12/2014/ኢዜአ/ ህዝብን ለማገልገል የገባነውን ቃል በተግባር ለማስቀጠል የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የምስራቅ አፍሪካ የባህልና የጥበብ ፌስቲቫል ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድርና ከተማ አቀፍ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ህዝብን በብቃትና በታማኝነት ማገልገል አለባቸው ብለዋል።

አዲስ አበባ የአብሮነት፣ የፍቅርና የአንድነት ከተማ መሆኗን የጠቀሱት ከንቲባዋ ሲቪል ሰርቫንቱ የአገልጋይነት ብቃቱን በማሳደግ ዝግጁነቱንም ማጠናከር አለበት ብለዋል።

ጤናን ለመጠበቅ የአካል ብቃት ስፖርት እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ጤናማና ብቁ በመሆን ህዝብን ለማገልገል የገባነውን ቃል በተግባር ለማስቀጠል የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ የዛሬው መርሃ ግብር በሁለቱም ፆታዎች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ተካሂዷል።

May be an image of one or more people, people standing, outdoors and crowd

በውድድሩ በወንዶች አትሌት ሌሊሳ አራርሳ አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን አትሌት ተሰማ መኮንን እና  አትሌት  ድንቃለም አየለ  በቅደም ተከተል የብርና የነሃስ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

በሴቶች በተደረገው ውድድር ደግሞ አትሌት አይናዲስ መብራቱ ቀዳሚ ስትሆን አትሌት አንቺንአሉ ደሴ እና አትሌት ፋንቱ  ሹጊ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በውድድሩ በሁለቱም ፆታ ለእያንዳንዳቸው አንደኛ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች የ15 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ ለወጡ የ13 ሺህ ብር እንዲሁም ሶስተኛ ለወጡት ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል።

በአትሌቶች መካከል የተደረገውን ውድድር የባህልና  ስፖርት  ሚኒስትሩ  ቀጀላ  መርዳሳ፤  በመገኘት አስጀምረውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም