በክልሉ ግብርናን በመካናይዜሽን በታገዘ ለማካሄድ እየተሰራ ነው

83

ሰኔ 12/2014 ጅግጅጋ/ኢዜአ/ በሶማሌ ክልል የግብርና ልማት በመካናይዜሽን በመታገዝ ለማካሄድ የእርሻ ትራክተሮችን ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ አስታወቁ።

የሶማሌ ክልል መንግሥት በክልሉ ለግብርና ልማት ምቹ የሆነውን ለም መሬት በዘመናዊ መካናይዜሽን ለማልማት የገዛቸውን 100 የእርሻ ትራክተሮች ትናንት በጅግጅጋ ከተማ ተረክቧል።

የክልሉ መንግሥት የተረከባቸው ትራክተሮች በዚህ ዓመት በ152 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ከወጠናቸው 162 የእርሻ ትራክተሮች ውስጥ መሆናቸውን በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

መንግስት በክልሉ ግብርናን በዘመናዊ መካናይዜሽን በታገዘ ለማካሄድ የእርሻ ተራክተሮችን ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችንና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀም  ከባህላዊ አሰራር ተላቀው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የከፊል አርሶ አደር ማህበረሰብን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮችን በማቅረብ በክልሉ የእርሻ መካናይዜሽን እንዲተገበር መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ማህበረሰብ በክልሉ ያለውን ለግብርና ስራ ተስማሚ የሆነውን ለም መሬት በስፋት እንዲያለማ የህዝብ ንቅናቄ እንዲፈጠር በማድረግ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ "በመዳፎቺህ ያለህ ውሃ የበለጠ ጥም ይቆርጣል" የሚለውን የሶማሊኛ ብሂል ጠቅሰው፤ መሬትን በሰብል መሸፈን ከእርዳታ ጥገኝነት እንደሚያላቅቅም አስረድተዋል።

የክልሉ ህዝብ ያለውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ የግብርና ምርታማነትን እንዲያሳድግ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበው፤ ይህም ለክልሉ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የክልሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብዲቃድር ኢማን እንዳሉት የእርሻ ትራክተሮቹ በክልሉ የግብርና ልማትን በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ የሚያግዙ ናቸው።

ትራክተሮቹ በሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ 50በመቶ ቅድመ ክፍያ ተፈጽሞ ቀሪው በአንድ ዓመት በሚከፈል ብድር ለከፊል አርሶ አደሮች የተላለፉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 62 ትራክተሮች በቅርቡ ይደርሳሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም