ግብርናውን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል -ቢሮው

89

ሚዛን ሰኔ 12/2014 (ኢዜአ)… በግብርናው ሜካናይዜሽን ላይ በትኩረት በመስራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ የቆየው የ2014/15 የግብርና ሜካናይዜሽን እና የመኸር እርሻ ተግባራት ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለጹት በግብርናው ዘርፍ የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በሃላፊነት ሊሰራ ይገባል።

የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየርና ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ጥረት በተለይም በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው ይህም ከተለመደው አሰራር በመውጣት ዘርፉን በሳይንስ ሲደገፍ ብቻ ለስኬት እንደሚደረስ መገንዘብ አለብን ብለዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን በመተግበርና አርሶ አደሩን ለዚያ ማብቃት ደግሞ ሁሉም አመራርና ባለሙያዎች በትኩረት ልሄዱበት የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮው መኸር እርሻ በክልሉ ከ326 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ይህ እንዲሳካም የዘርፉ አመራርና የዘርፉ ባለሙያዎች በቅንጅትና በቁርጠኝነት እንዲሁም አርሶ አደሩን በቅርበት በመደገፍ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተዘራ ወልደማርያም በበኩላቸው እንደሀገር እያጋጠመ ያለው የዘር አቅርቦትና የግብርና ግብአቶች እጥረት ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥት በኩል እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር በየአካባቢው አማራጭ መፍትሔዎችን በመጠቀም ስራውን ማስቀጠል እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን ሰፊ የእርሻ መሬት፣ የወሃ ሀብትና ጉልበት በአግባቡ አዋህዶ  በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል ።

በተለይ አመራሩ ከወትሮው የተሻለ የተግባር አፈጻጸም ማሳየት እንዳለበት ጠቅሰው በውጤት የታጀበ ስራ ለመስራት የተጀመረውን የግብርና ንቅናቄ ቀጣይነት ባለው መልኩ መምራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከመኸር እርሻ ጎን ለጎንም በክረምቱ የሚሰሩ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ወቅታዊ የግብርና ስራዎችን ለማሳካት የዘርፉ አካላት በንቃት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በዞኑ የመኸር እርሻ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተጀመረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የኩታ ገጠም እርሻ እየተለመደ መምጣቱን ጠቁመው በበልግ ከ10 ሺህ በላይ ሄክታር በኩታ ገጠም ለማረስ የታየውን መነቃቃት በመኸር እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

ከሰብልና ጥራጥሬ በተጨማሪ የፍራፍሬ ተከላ በመኸር ወቅት በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም