የቀጥታ ቡና ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ አድርጎናል - ቡና አቅራቢዎች

813

ሐዋሳ ሰኔ 12/2014 (ኢዜአ)፡ መንግስት በቡና ግብይቱ ላይ ያደረገው ለውጥ ለዓመታት ጥያቄያችን መልስ የሰጠና ተጠቃሚ ያደረገን ነው ሲሉ የቡና አቅራቢዎች ተናገሩ።

በግብይቱ ላይ የተደረገውን ለውጥ ቀጣይነት በማረጋገጥ  በዘርፉ የተገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።

ቡና አቅራቢዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት ቀጥተኛ የቡና ግብይት ስርዓት በመዘርጋቱ ለገበያ ካቀረቡት የቡና ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ቡና አቅራቢዎቹ ገለጻ በግብይቱ ላይ የተደረገው ለውጥ የተለያዩ አማራጮችን ያስቀመጠና ለዓመታት ጥያቄያቸው መልስ የሰጠ ነው፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቡና አቅራቢ ሃጂ ሙስጠፋ ከድር ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚደረገው የቡና ግብይት ባለቤት እንዳንሆን አድርጎን ቆይቷል ብለዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ቀጥተኛ የግብይት ስርዓት ከተለያዩ ላኪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ጥራት ያለው ቡና አምርተን በተሻለ ዋጋ እንድንሸጥ አደርጎናል ብለዋል፡፡

የግብይት አሰራር ለውጡ ከአርሶ አደር ጀምሮ እስከ ሀገር ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው ስሉ አብራርተዋል፡፡

ከግብይት ለውጡ በኋላ ከዚህ ቀደም ከሚያመርቱት የተሻለ ጥራትና ብዛት ያለው ቡና ማምረት መጀመራቸውን ገልጸው፤ዘንድሮው 148 ሺህ 750 ኪሎ ግራም ደረጃ 1 ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት ያቀርቡት የነበረው ቡና ከአሁኑ በሶስት እጥፍ ያንስ እንደነበርና ጥራቱም የወረደ መሆኑን አስታውሰዋል።

ከሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ ቡና አቅራቢው የሆኑት አቶ ታምራት ዮሴፍ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በነበረው የቡና ግብይት ተጠቃሚው ደላላው በመሆኑ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሰራሩ ከአምራቹ ጀምሮ ሀገርን ተጠቃሚ የማያደርግ እንደነበር የገለጹት ቡና አቅራቢው፤ በቡና ጥራት ላይ የነበረው ተጽዕኖም ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተጀመረው ቀጥታ ግብይት ግን አምራቹን አቅራቢውንና ላኪውን ፊት ለፊት ያገናኘና ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ሀገርንም ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''ከአርሶ አደሩ የተሰበሰበ ቡና እሸትነቱን ሳይጨርስ ከአቅራቢው ዘንድ ይደርሳል'' ያሉት አቶ ዮሴፍ  ቡና ጥራቱን ጠብቆ በተሸለ ዋጋ እንዲሸጥ እድል የፈጠረ የግብይት ስርዓት ነው ብለዋል፡፡

አቅራቢው እንደሚሉት አማራጭ የግብይት ስርዓት መዘርጋቱ ለረዥም ጊዜ ጥያቄቸው ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የቡና ጥራት እንዲጠበቅና በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ አድርጓል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ደረጃውን የጠበቀ 44 ሺህ ኪሎ ግራም ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

''ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከቡና ኪሳራ ተርፈናል'' ያሉት ደግሞ ከደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ በቡና አቅራቢነት የሚሰሩት አቶ ኢያሱ ዌራሳ ናቸው፡፡

የቡና ግብይቱ ከዚህ ቀደም ባለቤት አልነበረውም የሚሉት አቅራቢው አገናኞች ወይም ደላሎች ግብይቱን ስለሚቆጣጠሩት ሻጭና ገዥ አይተዋወቁም ነበር ብለዋል፡፡

አዲሱ የቡና ግብይት ስርዓት ከተጀመረ በኋላ ጥራቱን የጠበቀ ብዛት ያለው ቡና በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ በበኩላቸው የተገኘው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው እስከ ቀበሌ ድረስ የግብይት ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር የተገኘው ገቢ ከአምራች ገበሬው ጀምሮ በቡና የተሰማሩ አካላትንና ሀገርን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ባለስልጣኑ መረጃ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና የሚገኘው ገቢ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ሲሆን በመጪው ዓመት ደግሞ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅድ ተይዟል፡፡

ባለስልጣኑ ሰሞኑን በሐዋሳ አዘጋጅቶት በነበረው መድረክ ከደቡብ፣ ሲዳማና አሮሚያ ክልል አቅራቢዎች፣ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ከግብይት ለውጡ በኋላ በተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮቶች ላይ መምከሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም