ቤተክርስትያኗ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ያስገነባቻቸው ፕሮጀክቶች አገልግሎት ጀመሩ

90

ሐረር፣ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮዽያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጎሮ ጉቱ ወረዳ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ያስገነባቻቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

በቤተክርስትያኗ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ ግድብ ቦይ ዝርጋታ፣ የመጸዳጃ ቤትና የሶላር ሃይል ማመንጫ ናቸው።

በምስራቅ ሐረርጌ ካቶሊክ ሴክሬተርያት የማህበረሰብ ማጠናከርያና መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር በላይ አለማየሁ እንደተናገሩት፤ ከፕሮጀክቶቹ መካከል 3 ሺህ 400 አባወራዎችንና ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 175 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ ዓቅም ያላቸው ሶስት ታንከሮችና  ስምንት የውሃ ማከፋፈያ ቦኖ ይገኛል።

192 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከ200 ሄክታር መሬት በላይ ማልማት የሚችል ሶስት የመስኖ ግድብ ግንባታ እና ቦይ ዝርጋት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ለንጹህ መጠጥና መስኖ ልማት ስራ የሚያገለግል 32 ኪሎ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው የሶላር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም ተጠናቆ አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።

ለሁለት ትምህርት ቤቶች የመጸዳጃ ቤት ግንባታ መከናወኑን ዶክተር በላይ አክለው ገልጸዋል።

ቤተክርስትያኗ በተያዘው አመት በድሬዳዋ አስተዳደር፣ በጭናክሰን፣ ባቢሌ እና ደደር ወረዳዎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን እንዳከናወነች አስታውሰዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ ቤተክርስቲያኗ የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሰራችው ስራ ምስጋና አቅርበው፤ ፕሮጀክቶቹን የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

የቤተክርስትያኗ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የሃረርጌ አገረ ስብከት ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀ ዻዻስ አቡነ አንጀሎ ፓጋኖ በበኩላቸው ቤተክርስትያኗ ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የምታከናውነውን ተግባር እንደምታስቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም