ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ የምታስገባው ነዳጅ በሕገወጥ መልኩ እንዳይዘዋወር ክልሉ በትኩረት ይሰራል-- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

82

ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገሪቱ የምታስገባው ነዳጅ ለታለመለት አላማ እንዲውል ለማድረግ የሕገወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አመለከቱ።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቅርቡ ተግባራዊ በሚደረገው የነዳጅ ግብይት ድጎማ ላይ ከሀረሪ ክልል የመስተዳድር ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ተወካይ አቶ አህመድ ቱሳ ባቀረቡት ፅሁፍ በነዳጅ ግብይት ከታሪፍና የትርፍ ህዳግ ጋር የተያየዙ ችግሮች፣ የነዳጅ ግብይት መሰረተ ልማት እና ሎጂስቲክ ውስንነት፣ የአሰራር እና ቁጥጥር ማነስ በዘርፉ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

መንግስት ለነዳጅ እያደረገ ያለው ድጎማ ነዳጅን ለታለመለት አላማ ከማዋል ይልቅ ወደ ጎረቤት ሀገራት በማሸሽ ለህገወጦች እና ለኮትሮባንድ ነጋዴዎች በር የከፈተ በመሆኑ አሰራሩን በፖሊሲ መምራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም አብራርተዋል።

የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው አገሪቷ የምታስገባው ነዳጅ በህገወጥ መንገድ በጥቁር ገበያ ወደሌላ አካባቢ እየተጓዘ መሆነን ገልጸዋል፤ በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ እየቀረበ ያለው ነዳጅ ለታለመለት አላማ እንዲውል ህገ ወጥ የነዳጅ ዝውውርን በማስቆም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት ተቋማትም ከነዳጅ ውጪ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የነዳጅ ፍጆታን ማስተካከል እንደሚገባቸው ጠቁመው በተለይ አገሪቷ የምታስገባው ነዳጅ ለታለመለት አላማ እንዲውል ህገ ወጥ የነዳጅ ዝውውርን በማስቆሙ ረገድ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የንግድ እና ቀጠና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ እንደገለፁት ነዳጅ ከሁሉም ዘርፍ ጋር የሚገናኝ ቢሆንም ካሁን ቀደም የራሱ ደንብ እናመመሪያ ፖሊሲ ያልነበረው መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ዘርፉን እየደጎመ ለተጠቃሚዎች በአነስተኛ ዋጋ ነዳጅ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ በዚህም መንግስት 132 ቢሊዮን ብር እዳ ውስጥ የገባበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተው ከጊዜ ወደ ጊዜ የአለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በመሆኑ የነዳጅ አጠቃቀም ባህላችንን ኢኮኖሚያዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም