በከተማ ግብርና በመሰማራታችን የምግብ ፍጆታ ወጪያችንን ከማስቀረት ባለፈ ሌሎችን ማገዝ ጀምረናል

158

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በከተማ ግብርና በመሰማራታችን የምግብ ፍጆታ ወጪያቸውን ከመሸፈን ባለፈ ሌሎችን ማገዝ መጀመራቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ "ምግባችን ከጓሯችን" በሚል ሃሳብ ዜጎች ያገለገሉ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ጭምር በከተማ ግብርና እና የጓሮ አትክልት ልማት እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልት ልማት በማከናወን በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካማ ዜጎች ማዕድ ማጋራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና በመሳተፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ኢዜአ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በግቢያቸው የጓሮ አትክልት እያለሙ የሚገኙ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

አቶ ባህሩ አማን በግቢያቸው ለምግብነት የሚውሉ የጓሮ አትክልቶችን በስፋት በማምረት ቤተሰባቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከዚህ ቀደም ለምግብነት የሚውል አትክልት ለመግዛት ሲያወጡት የነበረውን ወጪ እንዳስቀረላቸው ነው የሚናገሩት፡፡

አቶ ለገሰ ተፈራ በበኩላቸው አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን በመጠቀም በአነስተኛ ቦታ የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጓሮ አትክልት ልማት በምግብ ራስን በመቻል ረገድ ትልቅ ውጤት እንዳስገኘላቸው ጠቅሰው፤ የመዲናዋ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና በመሳተፍ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለማስቻል የተያዘውን ውጥን እንዲሳካ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ወይዘሮ ብርቱካን ሙሉጌታ ወደ ከተማ ግብርና የገቡት በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ምክር መሆኑን በማንሳት፤ ባለሙያዎቹ አሁንም ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡ ቦታ የለንም የሚል ምክንያት ሳይፈጥር በቀላል መንገድ የጓሮ አትክልት በማልማት በምግብ ራሱን ለመቻል በቁርጠኝነት እንዲሰራም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ወይዘሮ አሚና ኢድሪስም በባለሙያዎች ድጋፍ በጓሮ አትክልት ልማት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ለምግብ ያወጡት የነበረውን ወጪ ማስቀረት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በከተማ ግብርና በመሳተፍ በምግብ ራሱን ከመቻል ባሻገር ጤናማ ምግብ ማግኘት እንደሚችልም ነው ያስረዱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም