ዩኒቨርሲቲው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ እየሰራ ነው

106

ባህር ዳር፤ ሰኔ 11/2014(ኢዜአ) የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው በባህር ዳር ከተማ ቤዛዊት ተራራ ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞች ትናንት ተጎብኝተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተቀዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር ተሰማ ዓይናለም እንደገለጹት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራውን በባህር ዳር ከተማ ዳርቻና በምዕራብ ጎጃም ዞን እያከናወነ ነው።

በባህር ዳር ከተማ ቤዛዊት ተራራና በዞኑ ይልማና ዴንሳ፣ቋሪት፣ ሰከላና ደቡብ ሜጫ ወረዳዎች በተለይ  "ብር አዳማ" በሚባል የተፋሰስ ቦታ በሚካሄደው ሥራ ወደ ዓባይ ወንዝ የሚገባ ደለልን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንደሚያስችሉ አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በአካባቢዎቹ  ለሚተክላቸው 600 ሺህ ችግኞች የጉድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከችግኞቹ 550 ሺህ የሚሆኑት በብር አዳማ፤ 50 ሺህ ችግኞች ደግሞ በቤዛዊት ተራራ እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

ከሚተከሉት ችግኞች መካከልም ኮሶ፣ ግራር፣ ዝግባ፣ ወይራ ይገኙበታል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተከላቸው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞች 75 በመቶው መጽደቃቸውን ገልጸዋል።

''በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ በላይ ተፈልቶ ለተከላ ተዘጋጅቷል'' ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ግብርናና መሬት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ አቶ ትልቅ ሰው እምባቆም ናቸው።

በመርሐ ግብሩ ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከላቸውንና ከነዚህም ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን በጥናት መረጋገጡንም ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ችግኞች  ከተከሉ በኋላ አስፈላጊውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲጸድቁ  ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በዚህም የሚተከሉ ችግኞች የመፅደቅ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ሃላፊው አስረድተዋል።

በከተማው አስተዳደር ከሚተከሉት ችግኞች ወይራ፣ዋንዛ፣ አቮካዶ፣ ቡናና ሙዝ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በጉብኝት ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም