የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ለአምስት አቅመ ደካማ አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ገንብተው አስረከቡ

94

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ለአምስት አቅመ ደካማ አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ገንብተው አስረከቡ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከ400 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት የገነቧቸውን መኖሪያ ቤቶች  23 የቤተሰብ አባላት ላሏቸው አምስት አቅመ ደካማ አባወራዎች አስረክበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ  መኖሪያ ቤቶቹን ለነዋሪዎቹ አስረክበዋል ።

ፕሬዝዳንቱ በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት ካለን በማካፈል አቅመ ደካሞችን በመርዳት ማህበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር ይገባል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያለበትን ማህበራዊ ሃላፊነት ለመወጣት በየዓመቱ ለአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት በመገንባትና በበዓላት ጊዜ ድጋፍ በማድረግ በጎ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በዚህ ዓመትም ከሠራተኞች በተዋጣ  ከ400 ሺህ ብር በላይ ለአምስት አቅመ ደካማ አባወራዎች የመኖሪያ ቤት መገንባቱን አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለው በከተማው አቅም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ካላቸው በማካፈል አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት እሴትን ሊያሳዩ እንደምገባ አመልክተዋል።

አቅመ ደካማን ለመርዳት ከሰብአዊነት ውጭ የተትረፈረፈ ሀብት አያስፈልግም " ያሉት ፕሬዝዳንቱ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ካላቸው በማካፈል ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በዋቢነት ጠቅሰዋል ።

የመኖሪያ ቤት ከተገነባላቸው አቅመ ደካሞች መካከል ወይዘሮ ንጋቷ አመኑ  ቤታቸው በማርጀቱ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች  ባደረጉት በጎ አስተዋፅኦ በተገነባላቸው መኖሪያ ቤት መደሰታቸውን ገልጸዋል ።

 "ስድስት የቤተሰብ አባላት ይዤ በየኪራይ ቤቱ  ስንገላታ ቆይቻለሁ"  ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፈቲያ ሳቢር ናቸው።

በተገነባላቸው የመኖሪያ ቤት እየገባ ካለው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ ከፈጠረባቸው ስጋት መላቀቃቸውን አመልክተዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም