መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማጠናቀቅ እንጂ አዲስ ፕሮጀክት የመጀመር እቅድ የለውም

79

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማጠናቀቅ እንጂ አዲስ ፕሮጀክት የመጀመር እቅድ እንደሌለው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

በ2014 በጀት ዓመት ሊጀመሩ ታቅደው በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባትም ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባው ለ2015 በጀት ዓመት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት መዘጋጀቱን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በጀቱን በሚመለከት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከ2015 ረቂቅ በጀት ውስጥ  347 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ እንዲሁም 218 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ መመደቡን ገልጸዋል።

የካፒታል በጀቱ ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ትኩረት እንደተሰጠውም ነው የጠቀሱት፡፡

የ2015 የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀትና የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በረቂቅ በጀቱ  ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማጠናቀቅ ደግሞ በረቂቅ በጀቱ ትኩረት እንደተሰጠው  ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት ምንም ዓይነት አዲስ የልማት ፕሮጀክት እንደማይጀምር ገልጸው፤ ረቂቅ በጀቱ እቅድ ወጥቶላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጀመሩ እንዲሁም ተጀምረው ላልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት ሊጀመሩ ታቅደው በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶች በ2015 በጀት ዓመት ሊጀመሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ከ2015 እስከ 2019 ዓ.ም. በተዘጋጀው የመካከለኛ የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍ መሰረት መንግሥት ፕሮጀክቶች የታቀደላቸውን ግብ እንዲያሳኩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በቀጣይ ለፕሮጀክቶች በጀት የሚመደበው ከአሥር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ጋር በማናበብ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በ2016 በጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር በመካከለኛ ዘመን ማዕቀፉ ተዘጋጅቷል  ነው ያሉት።

መንግሥት ከፕሮጀክት አፈጻጸም በተጓዳኝ ቁጠባ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ ተቋማትን በማዋሃድ እስከ 40 በመቶ ወጪን ለመቀነስ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ዶክተር ፍጹም አክለውም ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶች የሚታቀዱበትና የሚተዳደሩበት የሕግ መመሪያ እንዳልነበረ ጠቅሰው፤ በ2013 ዓ.ም የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር አዋጅ መጽደቁን ገልጸዋል።

አዋጁን መሰረት በማድረግም ፕሮጀክቶችን ከሀሳብ ቀረጻ ጀምሮ እስከ ግንባታ ፍጻሜ ድረስ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ክትትል እንደሚያደርጉ ነው የጠቀሱት።

በተለይም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት መከናወናቸውን ከተጠናቀቁ በኋላም የታለመላቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ስለማምጣታቸው በትኩረት እንደሚገመገምም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም