የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በጋሞ ዞን የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎበኙ

77

አርባምንጭ ፤ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ በጋሞ ዞን የልማት ማህበር እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።

ማህበሩ በተረከበው የእርሻ ማሳ እያከናወነ ያለው የግብርና ልማት እንቅስቃሴ አስደሳች መሆኑን መመልከታቸው አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

ልማት ማህበሩ እያከናወነ ከሚገኘው የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ ልምድ በመውሰድ ልማቱ በአካባቢው  ሊያሰፋ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም የከብት ማድለብ፣ወተት ላምና የዶሮ እርባታ ለማከናወን አካባቢው ምቹ መሆኑን ጠቁመው፤ለዘርፉ   ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ልማት ማህበሩ የሚያከናውናቸውን የግብርና የልማት ስራዎች በማስፋት ለአካባቢው አርሶ አደሮች የተሞክሮ ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአካባቢው የሚመረቱ የተለያዩ የፍራፍሬ ዓይነቶች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ገበያ ሊቀርቡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የጋሞ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የእርሻ ስራው የተሻለ ውጤት እንዲያስገኝና ዘርፉን በእውቀት ለመምራት በተማረ የሰው ኃይል የማደራጀት ስራ እየተከናወነ  መሆኑን ተናግረዋል ።

ማህበሩ ለእንስሳት እርባታና ለወተት ተዋፅኦ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የቦረና ዝሪያ ያላቸው የተወሰኑ የስጋ ከብቶችን የማድለብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የጋሞ ልማት ማህበር ከ778 ሄክታር በላይ ማሳ የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የልማት ማህበሩ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዋሻሮ ናቸው።

አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሾ በልማት ማህበሩ ከሚከመናወኑ የልማት ስራዎች  መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም